ኤርምያስ 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 “ ‘በዚያ ጊዜ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ የይሁዳ ነገሥታትና መኳንንት ዐፅም፣ የካህናትና የነቢያት ዐፅም፣ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዐፅም ከየመቃብራቸው ይወጣል። 2 በወደዷቸውና በአገለገሏቸው እንዲሁም በተከተሏቸው፣ ባማከሯቸውና ባመለኳቸው በፀሓይ፣ በጨረቃና በሰማያት ከዋክብት ሁሉ ፊት ይሰጣል፤ አይሰበሰብም ወይም አይቀበርም፤ ነገር ግን እንደ ተጣለ ጕድፍ በምድር ላይ ይበተናል። 3 ከዚህ ክፉ ሕዝብ የተረፉት ሁሉ፣ ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ፤ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።’ ኀጢአትና ያስከተለው ቅጣት 4 “እንዲህ በላቸው፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ሰዎች ቢውድቁ፣ እንደ ገና ከወደቁበት አይነሡምን? ሰው ተሳስቶ ወደ ኋላ ቢሄድ፣ ከስሕተቱ አይመለስምን? 5 ታዲያ፣ ይህ ሕዝብ ለምን ፊቱን አዙሮ ወደ ኋላ ይሄዳል? ለምንስ ኢየሩሳሌም ዘወትር ወደ ኋላ ትመለሳለች? ተንኰልን የሙጥኝ ብለው ይዘዋል፤ ሊመለሱም ፈቃደኛ አይደሉም። 6 እኔ በጥንቃቄ አደመጥኋቸው፤ ትክክለኛ የሆነውን ግን አይናገሩም። ማንም ስለ ክፋቱ ንስሓ የገባ የለም፤ “ምን አድርጌአለሁ?” ይላል። ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ፈረስ፣ እያንዳንዱ በራሱ መንገድ ይሄዳል። 7 ሽመላ እንኳ በሰማይ፣ የተወሰነ ጊዜዋን ታውቃለች፤ ዋኖስ፣ ጨረባና ዋርዳም፣ የሚሰደዱበትን ጊዜ ያውቃሉ፤ ሕዝቤ ግን፣ የእግዚአብሔርን ሥርዐት አላወቀም። 8 “ ‘የጸሓፊዎቻችሁ ሐሰተኛ ብርዕ ሐሰት እያስተናገደ እንዴት፣ “ዐዋቂዎች ነን፣ የእግዚአብሔር ሕግ አለን” ትላላችሁ? 9 ጥበበኞች ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉ፤ በወጥመድም ይያዛሉ። የእግዚአብሔርን ቃል ተቃውመው፣ ምን ዐይነት ጥበብ ይኖራቸዋል? 10 ስለዚህ ሚስቶቻቸውንም ለሌሎች ወንዶች እሰጣለሁ፤ ዕርሻዎቻቸውንም ለባዕዳን እሰጣለሁ፤ ከታናሹ እስከ ታላቁ ድረስ፣ ሁሉም ተገቢ ላልሆነ ጥቅም ይስገበገባሉ፤ ነቢያትና ካህናትም እንዲሁ፤ ሁሉም ያጭበረብራሉ። 11 የሕዝቤን ቍስል ብርቱ እንዳይደለ በመቍጠር፣ የተሟላ ፈውስ ሳይኖር እንዲሁ ያክማሉ፤ ሰላም ሳይኖር፣ “ሰላም፣ ሰላም” ይላሉ። 12 ስለ ጸያፉ ተግባራቸው ዐፍረዋል እንዴ? የለም! በጭራሽ አላፈሩም፤ ዕፍረት ምን እንደ ሆነ እንኳ አያውቁም። ስለዚህ ከወደቁት ጋራ ይወድቃሉ፤ በሚቀጡ ጊዜ ይዋረዳሉ፣ ይላል እግዚአብሔር። 13 “ ‘ያመረቱትን ሁሉ እወስድባቸዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ በወይን ተክል ላይ የወይን ፍሬ አይኖርም፤ በበለስ ዛፍ ላይ የበለስ ፍሬ አይገኝም፤ ቅጠሎቻቸውም ይረግፋሉ። የሰጠኋቸው በሙሉ፣ ከእነርሱ ይወሰድባቸዋል።’ ” 14 ለምን እዚህ እንቀመጣለን? በአንድነት ተሰብሰቡ! ወደ ተመሸጉት ከተሞች እንሽሽ፤ በዚያም እንጥፋ! በርሱ ላይ ኀጢአትን ስላደረግን፣ እግዚአብሔር አምላካችን እንድንጠፋ አድርጎናል፤ የተመረዘ ውሃ እንድንጠጣ ሰጥቶናል። 15 ሰላምን ተስፋ አደረግን፤ መልካም ነገር ግን አልመጣም፤ የፈውስ ጊዜን ተመኘን፤ ነገር ግን ሽብር ብቻ ሆነብን። 16 የጠላት ፈረሶች ፉርፉርታ፣ ከዳን ይሰማል፤ በድንጉላ ፈረሶቻቸው ማሽካካት፣ መላዋ ምድር ተንቀጠቀጠች። ምድሪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ፣ ከተማዪቱንና በውስጧ የሚኖሩትን ሁሉ፣ ሊውጡ መጡ። 17 “እነሆ፤ በመካከላችሁ መርዘኛ እባቦችን፣ የአስማተኛ ብልኀት የማይገታቸው እፉኝቶችን እሰድዳለሁ፤ እነርሱም ይነድፏችኋል፤” ይላል እግዚአብሔር። 18 በሐዘኔ የምታጽናናኝ ሆይ፤ ልቤ በውስጤ ዝላለች። 19 እንዲህ የሚለውን የሕዝቤን ጩኸት፣ ከሩቅ ምድር ስማ፤ “እግዚአብሔር በጽዮን የለምን? ንጉሧስ በዚያ አይኖርምን?” “በተቀረጹ ምስሎቻቸው፣ እንዲሁም ከንቱ በሆኑ ባዕዳን ለምን አስቈጡኝ?” 20 “መከሩ ዐለፈ፤ በጋው አበቃ፤ እኛም አልዳንም።” 21 ሕዝቤ ሲቈስል፣ እኔም ቈሰልሁ፤ አለቀስሁ፤ ድንጋጤ ያዘኝ። 22 በገለዓድ የሚቀባ መድኀኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም አልነበረምን? ለሕዝቤ ቍስል፣ ለምን ፈውስ አልተገኘም? |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.