ዘዳግም 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየሕዝቡ አለመታዘዝ 1 እስራኤል ሆይ፤ ስማ፤ ሰማይ ጠቀስ ቅጥር ያላቸው ታላላቅ ከተሞች ያሏቸውን፣ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ አስለቅቀህ ለመግባት ዮርዳኖስን አሁን ትሻገራለህ። 2 ዔናቃውያን ብርቱና ቁመተ ረዣዥም ሕዝቦች ናቸው፤ ስለ እነርሱ ታውቃለህ፤ “ዔናቃውያንን ማን ሊቋቋማቸው ይችላል?” ሲባልም ሰምተሃል። 3 ይሁን እንጂ እንደሚባላ እሳት ከፊትህ ቀድሞ የሚሻገረው አምላክህ እግዚአብሔር መሆኑን ዛሬ ርግጠኛ ሁን፤ እነርሱን ያጠፋቸዋል፤ በፊትህም ድል ያደርጋቸዋል፤ አንተም እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት ታስወጣቸዋለህ፤ በፍጥነትም ትደመስሳቸዋለህ። 4 አምላክህ እግዚአብሔር እነርሱን ከፊትህ ካስወጣቸው በኋላ በልብህ፣ “ይህችን ምድር እንድወርስ እግዚአብሔር ወደዚህ ያመጣኝ፣ ከጽድቄ የተነሣ ነው” አትበል። በዚህ አይደለም፤ እነዚህን አሕዛብ እግዚአብሔር ከፊትህ የሚያሳድዳቸው በክፋታቸው ምክንያት ነው። 5 ምድራቸውን ገብተህ የምትወርሳት ከጽድቅህ ወይም ከልብህ ቅንነት የተነሣ ሳይሆን፣ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ የማለላቸውን ቃል ለመፈጸም አምላክህ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ከክፋታቸው የተነሣ ከፊትህ ስለሚያባርራቸው ነው። 6 ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር ይህችን መልካም ምድር እንድትወርሳት የሚሰጥህ ከጽድቅህ የተነሣ አለመሆኑን አስተውል፤ አንተ ዐንገተ ደንዳና ነህና። የወርቁ ጥጃ 7 አምላክህን እግዚአብሔርን በምድረ በዳ እንዴት እንዳስቈጣኸው አስታውስ፤ ከቶም አትርሳ። ከግብጽ ከወጣህበት ዕለት አንሥቶ እዚህ ቦታ እስከ ደረስህበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅህ ነህ። 8 በኮሬብ እግዚአብሔርን ለቍጣ አነሣሣችሁት፤ እርሱም እናንተን ሊያጠፋችሁ እጅግ ተቈጣ። 9 እኔም የድንጋይ ጽላቱን፣ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ የገባውን የኪዳን ጽላት ለመቀበል ወደ ተራራው በወጣሁ ጊዜ፣ እህል ሳልበላ፣ ውሃም ሳልጠጣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ 10 በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላት እግዚአብሔር ሰጠኝ፤ በተሰበሰባችሁበት ዕለት እግዚአብሔር ከተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የነገራችሁ ትእዛዞች ሁሉ በእነርሱ ላይ ነበሩባቸው። 11 አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከተፈጸመ በኋላ፣ እግዚአብሔር ሁለቱን የድንጋይ ጽላት ማለትም የኪዳኑን ጽላት ሰጠኝ። 12 ከዚያም እግዚአብሔር፣ “ተነሣ፤ ከግብጽ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ረክሰዋልና ፈጥነህ ከዚህ ውረድ፤ እኔ ካዘዝኋቸው ፈጥነው ፈቀቅ ብለዋል፤ ቀልጦ የተሠራ ጣዖትም ለራሳቸው አበጅተዋል” ብሎ ነገረኝ። 13 ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ሕዝብ አይቼዋለሁ፤ በርግጥ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው፣ 14 አጠፋቸውና ስማቸውንም ከሰማይ በታች እደመስሰው ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ከእነርሱ ይልቅ ብርቱና ብዙ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” 15 ስለዚህ ተራራው በእሳት እየተቀጣጠለ ሳለ፣ ሁለቱን የቃል ኪዳን ጽላት በሁለቱም እጆቼ እንደ ያዝሁ ከተራራው ተመልሼ ወረድሁ። 16 በርግጥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠርታችሁ እንደ ነበር ተመለከትሁ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስልም ለራሳችሁ አበጃችሁ፤ እግዚአብሔር እናንተን ካዘዛችሁ መንገድ በፍጥነት ወጥታችሁ ነበር። 17 ስለዚህ ሁለቱን ጽላት ወስጄ ከእጆቼ አሽቀንጥሬ በፊታችሁ ሰባበርኋቸው። 18 ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን በመፈጸም ለቍጣ እንዲነሣሣ የሚያደርገውን ኀጢአት ሁሉ ስለ ሠራችሁ፣ እህል ውሃ ሳልቀምስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፋሁ። 19 እናንተን ሊያጠፋችሁ ክፉኛ ተቈጥቶ ነበርና፣ እኔም የእግዚአብሔርን ቍጣና መዓት ፈራሁ፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ገና ሰማኝ። 20 እግዚአብሔር አሮንን ሊያጠፋው ክፉኛ ተቈጥቶ ነበር፤ በዚያ ጊዜ ለአሮንም ጸለይሁ። 21 ደግሞም ያን የኀጢአት ሥራችሁን፣ ያበጃችሁትን ጥጃ ወስጄ በእሳት አቃጠልሁት፤ ከዚያም ሰባብሬ እንደ ትቢያ ዱቄት እስኪሆን ድረስ ፈጭቼ ከተራራው በሚወርደው ጅረት ውስጥ በተንሁት። 22 በተቤራም፣ በማሳህና በቂብሮት ሃታአባ እግዚአብሔርን አስቈጣችሁት። 23 እግዚአብሔር ከቃዴስ በርኔ ባስወጣችሁ ጊዜ፣ “ውጡ፤ የሰጠኋችሁንም ምድር ርስት አድርጋችሁ ውረሷት” አላችሁ። እናንተ ግን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ፤ እርሱን አልታመናችሁበትም፤ አልታዘዛችሁትምም። 24 እኔ እናንተን ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ፣ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ። 25 እግዚአብሔር እናንተን እንደሚያጠፋችሁ ተናግሮ ስለ ነበር፣ በእነዚያ አርባ ቀናትና አርባ ሌሊቶች በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፋሁ፤ 26 እንዲህም በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ በታላቅ ኀይልህ የተቤዠኸውንና በኀያል ክንድህ ከግብጽ ያወጣኸውን፣ ያንተ ርስት የሆነውን ሕዝብህን አታጥፋ። 27 ባሪያዎችህን አብርሃምን፣ ይሥሐቅንና ያዕቆብን ዐስብ፤ የዚህን ሕዝብ ልበ ደንዳናነት፣ ክፋትና ኀጢአት አትመልከት። 28 አለዚያ እኛን ካመጣህበት ምድር ያሉ ሰዎች ‘እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ሊያገባቸው ስላልቻለና ስለ ጠላቸው፣ በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው’ ይላሉ። 29 ነገር ግን እነርሱ በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.