ዘዳግም 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበምድረ በዳ መንከራተት 1 ከዚያም እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት ተመለስን፤ ቀይ ባሕርን ይዘን ወደ ምድረ በዳው ተጓዝን፤ በሴይር ኰረብታማ አገር ዙሪያ ለረዥም ጊዜ ተንከራተትን። 2 ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ 3 “በዚህ በኰረብታማ አገር ዙሪያ እስኪበቃችሁ ተንከራታችኋል፤ አሁን ግን ወደ ሰሜን ተመለሱ። 4 ለሕዝቡም እነዚህን ትእዛዞች ስጣቸው፤ ‘ሴይር በሚኖሩት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ዘሮች ግዛት ዐልፋችሁ ትሄዳላችሁ፤ እነርሱ ይፈሯችኋል፤ ቢሆንም ከፍ ያለ ጥንቃቄ አድርጉ። 5 ከየትኛውም ምድራቸው ላይ ለጫማችሁ መርገጫ ታኽል እንኳ መሬት ስለማልሰጣችሁ፣ ለጦርነት አታነሣሧቸው። ኰረብታማውን የሴይርን አገር ርስት አድርጌ ለዔሳው ሰጥቼዋለሁ። 6 ከዚያ ለምትበሉት ምግብም ሆነ ለምትጠጡት ውሃ በጥሬ ብር ትከፍሏቸዋላችሁ።’ ” 7 አምላካችሁ እግዚአብሔር በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኳችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጕዞ ጠብቋችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም። 8 ስለዚህ በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮች የሆኑ ወንድሞቻችንን ዐልፈናቸው ሄድን። ከኤላትና ከዔጽዮንጋብር ከሚመጣው ከዓረባ መንገድ ተመልሰን፣ በሞዓብ ምድረ በዳ መንገድ ተጓዝን። 9 ከዚያም እግዚአብሔር፣ “ከሞዓባውያን ምድር አንዳችም መሬት ስለማልሰጣችሁ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሧቸው፤ ዔርን ለሎጥ ዘሮች ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ” አለኝ። 10 በዚያም ጠንካራና ቍጥራቸው የበዛ እንዲሁም እንደ ዔናቃውያን ረዣዥም የሆኑ ኤሚማውያን ይኖሩ ነበር። 11 እነዚህም እንደ ዔናቃውያን ሁሉ ራፋይማውያን ናቸው ተብለው ይገመቱ ነበር፤ ሞዓባውያን ግን ኤሚማውያን ብለው ይጠሯቸዋል። 12 ሖሪውያን ቀድሞ በሴይር ይኖሩ ነበር፤ የዔሳው ዘሮች ግን ከዚያ አሳድደው አስወጧቸው። እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሰጠው ምድር ላይ እስራኤል እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህም ሖሪውያንን ከፊታቸው አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ። 13 ከዚያም እግዚአብሔር “አሁኑኑ ተነሡና የዘሬድን ደረቅ ወንዝ ተሻገሩ” አለን፤ እኛም ወንዙን ተሻገርን። 14 ቃዴስ በርኔን ከለቀቅንበት ጊዜ አንሥቶ የዘሬድን ደረቅ ወንዝ እስከ ተሻገርንበት ጊዜ ድረስ ሠላሳ ስምንት ዓመት ዐለፈ። በዚያ ጊዜም ለጦርነት ብቁ የሆኑት የዚያ ትውልድ ወንዶች ሁሉ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ አስቀድሞ በማለው መሠረት ከሰፈሩ ፈጽመው ዐለቁ። 15 ከሰፈር ፈጽሞ እስኪያጠፋቸውም ድረስ የእግዚአብሔር እጅ በእነርሱ ላይ ነበር። 16 በሕዝቡ መካከል የነበሩት የመጨረሻዎቹ ተዋጊዎች ከሞቱ በኋላ፣ 17 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ 18 “የሞዓብ ዳርቻ ዔርን ዛሬውኑ ታልፋላችሁ። 19 ከየትኛውም የአሞናውያን ምድር ለእናንተ ርስት ስለማልሰጣችሁ፣ አሞናውያን ዘንድ በደረሳችሁ ጊዜ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሧቸው። ያን ቦታ ርስት አድርጌ ለሎጥ ዘሮች ሰጥቻቸዋለሁ።” 20 ያም ደግሞ በዚያ ይኖሩ የነበሩት የራፋይማውያን ምድር እንደ ሆነ ይቈጠር ነበር፤ አሞናውያን ግን ዘምዙማውያን ብለው ይጠሯቸው ነበር። 21 ዘምዙማውያን ብርቱዎች፣ ቍጥራቸው የበዛና እንደ ዔናቃውያን ቁመተ ረዣዥሞች ነበሩ፤ እግዚአብሔር ከእነርሱ ፊት አጠፋቸው፤ እነርሱም አሳደዷቸው፤ በምትካቸውም ሰፈሩበት። 22 እግዚአብሔር ሖሪውያንን ከፊታቸው ባጠፋ ጊዜ፣ በሴይር ለሚኖሩት የዔሳው ዘሮች ያደረገው ይህንኑ ነበር። እነርሱም አሳድደው በማስወጣት ባስለቀቁት ስፍራ ላይ እስከ ዛሬ ይኖራሉ። 23 እስከ ጋዛ ድረስ ባሉት መንደሮች የኖሩትን ኤዋውያን በተመለከተም፣ ከቀፍቶር ወጥተው የመጡት ከቀፍቶሪማውያን፣ እነርሱን አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ። የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን ድል መነሣት 24 “አሁኑኑ ተነሡና የአርኖንን ወንዝ ተሻገሩ፤ እነሆ፤ የሐሴቦንን ንጉሥ፣ አሞራዊውን ሴዎንንና አገሩን በእጃችሁ ሰጥቻችኋለሁ፤ ምድሩን መውረስ ጀምሩ፤ ጦርነት ግጠሙት። 25 ከሰማይ በታች ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ፣ ማስደንገጣችሁና ማስፈራታችሁ እንዲያድርባቸው ከዚህች ከዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ። ስለ እናንተ ሰምተው ይርበተበታሉ፤ ከእናንተ የተነሣም ይጨነቃሉ።” 26 ከቅዴሞት ምድረ በዳም ለሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን የሰላም ቃል እንዲያደርሱለት እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላክሁ፤ 27 “በአገርህ አቋርጠን እንድናልፍ ፍቀድልን፤ ከዋናው መንገድ አንወጣም፤ ቀኝም ግራም አንልም። 28 የምንበላውን ምግብ፣ የምንጠጣውንም ውሃ በጥሬ ብር ሽጥልን። በእግር እንድናልፍ ብቻ ፍቀድልን፤ 29 በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮችና በዔር የሚኖሩ ሞዓባውያን እንዳደረጉልን ሁሉ፣ አንተም አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን እስክንሻገር ድረስ እንደዚሁ አድርግልን።” 30 ይሁን እንጂ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን እንድናልፍ አልፈቀደልንም፤ ምክንያቱም አምላካችሁ እግዚአብሔር አሁን እንዳደረገው ሁሉ እርሱን በእጃችሁ አሳልፎ ለመስጠት መንፈሱን አደንድኖት፣ ልቡንም አጽንቶት ነበር። 31 እግዚአብሔርም፣ “እነሆ፤ ሴዎንንና አገሩን ለእናንተ አሳልፌ ልሰጣችሁ ተነሥቻለሁ፤ አሁንም እርሱን አሸንፋችሁ ምድሩን ለመውረስ ተነሡ” አለኝ። 32 ሴዎንና መላው ሰራዊቱ በያሀጽ ጦርነት ሊገጥሙን በወጡ ጊዜ፣ 33 አምላካችን እግዚአብሔር በእጃችን ላይ ጣለው፤ እኛም፣ እርሱን ከወንድ ልጆቹና ከመላው ሰራዊቱ ጋራ አንድ ላይ መታነው። 34 በዚያ ጊዜ ከተሞቹን በሙሉ ወስደን የሚኖሩባቸውን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆቻቸውን ጭምር ፈጽመን አጠፋናቸው፤ አንዳቸውንም በሕይወት አላስቀረንም። 35 ከብቶቻቸውንና ከየከተሞቻቸው ያገኘነውን ምርኮ ግን ለራሳችን አደረግን። 36 በአርኖን ሸለቆ ጫፍ ካለችው ከአሮዔርና በሸለቆው ውስጥ ከምትገኘዋ ከተማ አንሥቶ እስከ ገለዓድ ካሉት ከተሞች አንዳቸውም እንኳ ሊገቱን አልቻሉም። አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉንም አሳልፎ ሰጠን። 37 ይሁን እንጂ አምላካችን እግዚአብሔር በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ ወደ ማንኛውም የአሞናውያን ምድር ወይም በያቦቅ ወንዝ መውረጃ ወዳለው ምድር ወይም ደግሞ በኰረብቶች ወዳሉት ከተሞች ዙሪያ ዐልፋችሁ አልሄዳችሁም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.