2 ነገሥት 16 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየይሁዳ ንጉሥ አካዝ 16፥1-20 ተጓ ምብ – 2ዜና 28፥1-27 1 የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ፣ የኢዮአታም ልጅ አካዝ ነገሠ። 2 አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። አባቱ ዳዊት ያደረገውን መልካም ነገር በእግዚአብሔር ፊት አላደረገም። 3 እርሱም በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ያስወገዳቸውን የአሕዛብን ርኩሰት ተከትሎ፣ ልጁን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። 4 በኰረብታ ላይ ባሉ ማምለኪያ ስፍራዎችና በተራሮች ዐናት ላይ፣ በየዛፉም ጥላ ሥር መሥዋዕት አቀረበ፤ ዕጣንም ዐጠነ። 5 የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ለመውጋትና አካዝን ለመክበብ ወጡ፤ ይሁን እንጂ ሊያሸንፉት አልቻሉም። 6 በዚያ ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የይሁዳን ሰዎች አሳድዶ፣ ኤላትን ወደ ሶርያ ግዛት መለሰ፤ ከዚያም ኤዶማውያን ወደ ኤላት መጥተው እስከ ዛሬ በዚያ ይኖራሉ። 7 ከዚህ የተነሣም አካዝ፣ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር፣ “እኔ አገልጋይህም ልጅህም ነኝ፤ ስለዚህ መጥተህ ከሚወጉኝ ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ” ሲል መልእክተኞች ላከበት። 8 አካዝም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብርና ወርቅ ዘርፎ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት እንዲሆን ላከለት። 9 የአሦር ንጉሥም፣ የአካዝን ልመና በመቀበል፤ ደማስቆን አጥቅቶ ያዛት፤ ሕዝቧን ማርኮ ወደ ቂር አፈለሳቸው፤ ረአሶንንም ገደለው። 10 ከዚያም ንጉሥ አካዝ የአሦርን ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶርን ለመገናኘት ወደ ደማስቆ ሄደ። በደማስቆም ያለውን መሠዊያ አይቶ፣ ንድፉን ከዝርዝር ጥናቱ ጋራ ለካህኑ ለኦርያ ላከለት። 11 ካህኑ ኦርያም ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ በላከለት ዝርዝር ጥናት መሠረት መሠዊያ ሠራ፤ ንጉሡ አካዝ ከመመለሱም በፊት አጠናቀቀው። 12 ንጉሡ ከደማስቆ ተመልሶ በመጣ ጊዜ፣ መሠዊያውን አየ፤ ቀርቦም በመሠዊያው ላይ ወጣ፤ 13 ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕቱንና የእህል ቍርባኑን በመሠዊያው ላይ አቀረበ፤ የመጠጥ ቍርባኑን አፈሰሰ፤ የኅብረት መሥዋዕቱንም ደም በመሠዊያው ላይ ረጨ። 14 በአዲሱ መሠዊያና በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መካከል፣ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ የነበረውን የናስ መሠዊያ፣ ከቦታው አስነሥቶ ከአዲሱ መሠዊያ በስተሰሜን በኩል አኖረው። 15 ከዚያም ንጉሥ አካዝ፣ ካህኑን ኦርያን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በዚህ በትልቁ አዲስ መሠዊያ ላይ የጧቱን የሚቃጠል መሥዋዕትና የማታውን የእህል ቍርባን፣ የንጉሡን የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን እንዲሁም የመላውን የአገሪቱን ሕዝብ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህልና የመጠጥ ቍርባናቸውን አቅርብ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ደምና የሌላውን መሥዋዕት ደም ሁሉ በመሠዊያው ላይ ርጨው፤ የናሱ መሠዊያ ግን እኔ መመሪያ ለመጠየቅ የምጠቀምበት ይሆናል።” 16 ካህኑ ኦርያም ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ። 17 ንጉሡ አካዝም የጐንና የጐን ሳንቃዎቹን ነቅሎ ወሰደ፤ በተንቀሳቃሹ መቆሚያ ላይ ያሉትን የመታጠቢያ ሳሕኖች አስወገደ። የውሃ ማጠራቀሚያውን ክብ ገንዳ ከታች ተሸክመው ከያዙት ከዐሥራ ሁለቱ የናስ ቅርጽ ኰርማዎች ላይ አውርዶ በጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ አስቀመጠው። 18 የአሦርንም ንጉሥ ለማስደሰት ሲል፣ በዕለተ ሰንበት ንጉሣዊ ዙፋን እንዲዘረጋበት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የተሠራውን ከፍ ያለ ስፍራና ነገሥታቱ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚገቡበትን በውጭ ያለውን መግቢያ አነሣ። 19 በአካዝ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባርና የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 20 አካዝም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ከእነርሱ ጋራ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ሕዝቅያስም በምትኩ ነገሠ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.