2 ነገሥት 14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ 14፥8-22 ተጓ ምብ – 2ዜና 25፥17–26፥2 1 የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ። 2 በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 3 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ዐይነት አልነበረም፤ በማናቸውም ረገድ የአባቱን የኢዮአስን ፈለግ ተከተለ። 4 በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር። 5 መንግሥቱም በእጁ ከጸናለት በኋላ፣ ንጉሡን አባቱን የገደሉትን ሹማምት ገደላቸው። 6 ይሁን እንጂ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ እግዚአብሔር፣ “ሰው ሁሉ በገዛ ኀጢአቱ ይሙት እንጂ ወላጆች በልጆቻቸው አይገደሉ፣ ልጆችም በወላጆቻቸው ኀጢአት አይገደሉ” ሲል ያዘዘ በመሆኑ፣ የነፍሰ ገዳዩን ልጆች አልገደላቸውም። 7 የጨው ሸለቆ በተባለው ቦታ ዐሥር ሺሕ ኤዶማውያንን ድል ያደረገ፣ ሴላን በጦርነት የያዘና እስከ ዛሬም ድረስ ዮቅትኤል ተብላ የምትጠራበትን ስም ያወጣላት አሜስያስ ነው። 8 ከዚያም አሜስያስ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ዮአስ፣ “ናና ፊት ለፊት እንጋጠም” ሲል መልእክተኞች ላከበት። 9 የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ግን ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ለአንድ የሊባኖስ ዝግባ፣ ‘ሴት ልጅህን ለልጄ ሚስት እንድትሆነው ስጠው’ አለው፤ ከዚያም አንድ የሊባኖስ ዱር አውሬ መጥቶ ኵርንችቱን በእግሩ ረገጠው። 10 በርግጥ ኤዶምን ድል አድርገሃል፤ ልብህ በትዕቢት ተወጥሯል። ክብርህን ጠብቀህ ዐርፈህ በቤትህ ተቀመጥ! ጠብ በመጫር በራስህና በይሁዳ ላይ ውድቀት ለማምጣት ችግር የምትፈጥረው ለምንድን ነው?” 11 አሜስያስ ግን አልሰማም፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ምድር በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ተጋጠሙ። 12 ይሁዳ በእስራኤል ድል ሆነ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 13 የእስራኤል ንጉሥ ዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአስን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማረከው። ከዚያም ዮአስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ከኤፍሬም ቅጥር በር አንሥቶ የማእዘን ቅጥር በር እስከ ተባለው ድረስ ርዝመቱ አራት መቶ ክንድ ያህል ርዝመት ያለውን የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ። 14 በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች ያለውን ወርቅ ብርና ዕቃ በሙሉ፣ በዚያም የተገኘውን ዕቃ ሁሉ በመውሰድ ምርኮኞችንም ይዞ ወደ ሰማርያ ተመለሰ። 15 በዮአስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያደረገው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 16 ዮአስ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋራ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮርብዓምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። 17 የኢዮአስ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ ዐሥራ ዐምስት ዓመት ኖረ። 18 በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 19 አሜስያስ በኢየሩሳሌም ሤራ ስለ ጠነሰሱበት ሸሽቶ ወደ ለኪሶ ሄደ፤ እነርሱ ግን የሚከታተሉትን ሰዎች ወደ ለኪሶ ላኩ፤ እነርሱም ገደሉት፤ 20 አስከሬኑን በፈረስ ጭነው አመጡ። እንደ አባቶቹም ሁሉ በዳዊት ከተማ፣ በኢየሩሳሌም ተቀበረ። 21 ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የሆነውን ዓዛርያስን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፈንታ አነገሡት። 22 ንጉሥ አሜስያስ ከአባቶቹ ጋራ ካንቀላፋ በኋላ ኤላትን እንደ ገና ሠርቶ ወደ ይሁዳ የመለሳት ይኸው ዓዛርያስ ነበር። የእስራኤል ንጉሥ ዳግማዊ ኢዮርብዓም 23 የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ ዐምስተኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ ነገሠ፤ አርባ አንድ ዓመትም ገዛ። 24 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም። 25 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በጋትሔፌር ነቢይ፣ በአማቴ ልጅ በባሪያው በዮናስ አማካይነት እንደ ተናገረው፣ ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ እስከ ሙት ባሕር ድረስ የነበረውን የእስራኤልን ድንበር አስመለሰ። 26 ባሪያም ይሁን ነጻ፣ በእስራኤል የሚኖር ሁሉ በመራር ሥቃይ እንዴት እንደ ኖረ፣ እስራኤልንም የሚረዳ እንዳልነበረ፣ እግዚአብሔር አየ። 27 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የእስራኤልን ስም ከምድረ ገጽ እንደሚያጠፋ ስላልተናገረ፣ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም አማካይነት ታደጋቸው። 28 በኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር፣ የፈጸመው ሁሉና ያደረጋቸው ጦርነቶች እንዲሁም የይሁዳ ግዛት የነበሩትን ደማስቆንና ሐማትን እንዴት ለእስራኤል እንዳስመለሰ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 29 ኢዮርብዓም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ዘካርያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.