2 ነገሥት 13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየእስራኤል ንጉሥ ኢዮአካዝ 1 የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት፣ የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ሰባት ዓመትም ገዛ። 2 እርሱም የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ያሳተበትን ኀጢአት በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ ከዚህ ድርጊቱም አልተመለሰም። 3 የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ አዛሄልና ልጁ ቤን ሃዳድ በነበሩበት ዘመን ሁሉ አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው። 4 ከዚያም ኢዮአካዝ እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን እንዴት አድርጎ እንዳስጨነቀ አይቷልና ልመናውን ሰማው። 5 ስለዚህ እግዚአብሔር ለእስራኤል የሚታደጋቸውን ሰው ሰጠ፤ እነርሱም ከሶርያውያን ጭቈና ተላቀቁ፤ እንደ ቀድሞውም በየድንኳናቸው መኖር ጀመሩ፤ 6 ይሁን እንጂ እስራኤልን ከአሳተው ከኢዮርብዓም ቤት ኀጢአት አልተመለሱም፤ በዚያው ገፉበት እንጂ። የአሼራም ምስል ዐምድ በሰማርያ መመለኩ ቀጠለ። 7 ከኢዮአካዝ ሰራዊት የተረፈው ዐምሳ ፈረሰኞች፣ ዐሥር ሠረገሎችና ዐሥር ሺሕ እግረኛ ወታደር ብቻ ነው፤ ይህ የሆነበትም ምክንያት የሶርያ ንጉሥ የቀረውን ስለ አጠፋውና እንደ ዐውድማ ብናኝ ስለ አደረገው ነበር። 8 ኢዮአካዝ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላው ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 9 ኢዮአካዝ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ። ልጁ ዮአስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ 10 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ዘመን፣ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ስድስት ዓመትም ገዛ። 11 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ከአሳተበት ኀጢአት ሁሉ አልራቀም፤ በዚያው ገፋበት። 12 ዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላ ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያካሄደው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 13 ዮአስም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓም በእግሩ ተተክቶ በዙፋኑ ተቀመጠ። ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋራ ተቀበረ። 14 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ ለሞት ባደረሰው ሕመም ታምሞ ነበር። የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ወርዶ አለቀሰለት፤ “ወየው አባቴን! ወየው አባቴን! ወየው የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች!” እያለም ጮኸ። 15 ኤልሳዕም፣ “አንድ ቀስትና ፍላጾች አምጣ” አለው፤ እርሱም አመጣ፤ 16 የእስራኤልንም ንጉሥ፣ “ቀስቱን በእጅህ ያዘው” አለው፤ ቀስቱን በያዘውም ጊዜ ኤልሳዕ እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ። 17 ቀጥሎም፣ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለው፤ ከፈተውም፤ ኤልሳዕም፣ “በል አስፈንጥረው” አለው፤ አስፈነጠረውም፤ ከዚያም፣ “የእግዚአብሔር የድል ቀስት! ሶርያ ድል የምትሆንበት ቀስት!” አለ። ኤልሳዕም እንደ ገና “ሶርያውያንንም አፌቅ ላይ ፈጽመህ ድል ታደርጋቸዋለህ” አለው። 18 ቀጥሎም፣ “በል ቀስቶቹን ውሰድ” አለው፤ የእስራኤልም ንጉሥ ወሰደ። ኤልሳዕም፣ “መሬቱን ውጋ” አለው፤ እርሱም ሦስት ጊዜ ወግቶ አቆመ። 19 የእግዚአብሔርም ሰው ተቈጣውና፣ “መሬቱን ዐምስት ወይም ስድስት ጊዜ መውጋት ነበረብህ፤ እንዲህ ብታደርግ ኖሮ ሶርያን ታሸንፍና ፈጽመህ ትደመስሳት ነበር፤ አሁን ግን የምታሸንፈው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው” አለው። 20 ኤልሳዕ ሞተ፤ ቀበሩትም። በዚህም ጊዜ ሞዓባውያን አደጋ ጣዮች በየዓመቱ በጸደይ ወራት ወደ እስራኤል ምድር እየሰረጉ ይገቡ ነበር። 21 አንድ ጊዜ እስራኤላውያን ሰው ሞቶ ሲቀብሩ፣ አንድ የአደጋ ጣይ ቡድን በድንገት አዩ፤ ስለዚህ የሞተውን ሰው ሬሳ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ ጣሉት፤ ሬሳው የኤልሳዕን ዐፅም እንደ ነካም ወዲያውኑ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ። 22 በኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ሁሉ፣ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል፣ እስራኤልን ያስጨንቃቸው ነበር። 23 እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፤ ዐዘነላቸው፤ ፊቱን መለሰላቸው፤ ይህም ከአብርሃም፣ ከይሥሐቅና ከያዕቆብ ጋራ ስለ ገባው ኪዳን ሲል ነው፤ እስከ ዛሬ ድረስ ሊያጠፋቸው አልፈለገም፤ ከፊቱም አላስወገዳቸውም። 24 የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁ ቤን ሃዳድም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። 25 ከዚያም የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ፣ አዛሄል ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በጦርነት የወሰዳቸውን ከተሞች ከአዛሄል ልጅ ከቤን ሃዳድ አስመልሶ ያዘ። ዮአስ ሦስት ጊዜ ድል አደረገው፤ የእስራኤልንም ከተሞች በዚህ ሁኔታ መልሶ ያዘ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.