Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


2 ነገሥት 12 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን ዐደሰ
12፥1-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 24፥1-14 ፤ 24፥23-27

1 ኢዩ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ ነገሠ፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አርባ ዓመት ገዛ። እናቱ ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች።

2 ካህኑ ዮዳሄ ያስተምረው በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።

3 ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።

4 ኢዮአስ ካህናቱን እንዲህ አላቸው፤ “ከሕዝብ ቈጠራ የተገኘውንና በስእለት የገባውን እንዲሁም በራስ ፈቃድ ለእግዚአብሔር ቤት የተሰጠውን የተቀደሰ ገንዘብ በሙሉ ሰብስቡ።

5 እያንዳንዱም ካህን ገንዘቡን ከገንዘብ ያዡ እጅ ይቀበል፤ እንደ አስፈላጊነቱም በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ለማደስ ይዋል።”

6 ይሁን እንጂ እስከ ሃያ ሦስተኛው የኢዮአስ ዘመነ መንግሥት ካህናቱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን አላደሱም ነበር።

7 ስለዚህ ንጉሡ ኢዮአስ ካህኑን ዮዳሄንና ሌሎቹን ካህናት ጠርቶ፣ “በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ያላደሳችሁት ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው፤ ቀጥሎም፣ “ከእንግዲህ ወዲያ ገንዘቡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ለማደስ ይዋል እንጂ ከገንዘብ ያዦች አትቀበሉ” አላቸው።

8 ካህናቱም ከእንግዲህ ከሕዝቡ ገንዘብ ላለመሰብሰብና ቤተ መቅደሱንም ራሳቸው ላለማደስ ተስማሙ።

9 ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ በመክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀለት፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚያስገባው በስተቀኝ በኩል በመሠዊያው አጠገብ አኖረው። በራፉን የሚጠብቁት ካህናትም ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ በሣጥኑ ውስጥ ያስገቡ ነበር።

10 በሣጥኑም ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ፣ የንጉሡ ጸሓፊና ሊቀ ካህናቱ መጥተው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ ቈጥረው በየከረጢቱ በማስገባት ቋጥረው ያኖሩት ነበር።

11 የገንዘቡ ልክም ተመዝኖ ከታወቀ በኋላ፣ የቤተ መቅደሱን ሥራ በኀላፊነት እንዲያሠሩ ለተመደቡት ሰዎች ገንዘቡን ያስረክቧቸዋል፤ ይህም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለሚሠሩ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ግንበኞች፣

12 ለድንጋይ ጠራቢዎችና ለድንጋይ ቅርጽ አውጭዎች የሚከፈል፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለሚታደስበት ዕንጨትና ጥርብ ድንጋይ መግዣ የሚውል ነበር።

13 ለቤተ መቅደሱ ከገባው ገንዘብ ግን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግልጋሎት ለሚውሉ የብር ጽዋዎች፣ መኰስተሪያዎች፣ ድስቶች፣ መለከቶችና ወይም ለሌሎች የወርቅም ሆነ የብር ዕቃዎች መሥሪያ አልዋለም፤

14 የተከፈለው ግን የእግዚአብሔርን ቤት ለሚያድሱ ሠራተኞች ብቻ ነበር።

15 ለሠራተኞቹ እንዲከፍሉ ገንዘቡ የተሰጣቸው ሰዎች ፍጹም ታማኞች በመሆናቸው ተቈጣጣሪ ማድረግ አላስፈለጋቸውም ነበር።

16 ስለ በደል መሥዋዕትና ስለ ኀጢአት መሥዋዕት የሚቀርበው ገንዘብ ግን የካህናቱ በመሆኑ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይገባም ነበር።

17 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ወጣ፤ ጋትንም አደጋ ጥሎ ያዛት። ከዚያም በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ፊቱን አዞረ።

18 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ ግን አባቶቹ የይሁዳ ነገሥታት ኢዮሣፍጥ፣ ኢዮራም፣ አካዝያስ ለእግዚአብሔር ቀድሰው የለዩአቸውን የተቀደሱ ዕቃዎች በሙሉ፣ እርሱ ራሱ የቀደሳቸው ስጦታዎች እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ሰብስቦ ለሶርያ ንጉሥ ለአዛሄል ላከለት፤ አዛሄልም ከኢየሩሳሌም ተመለሰ።

19 ኢዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላው ተግባርና የፈጸመው ሥራ ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

20 ሹማምቱም በርሱ ላይ ዐመፁበት፤ ቍልቍል ወደ ሲላ በሚወስደው መንገድ ላይ በቤት ሚሎ ገደሉት።

21 ገዳዮቹ ሹማምትም የሰምዓት ልጅ ዮዛካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት ነበሩ። እርሱም ሞተ፤ እንደ አባቶቹም ሁሉ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አሜስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Siga-nos em:



Anúncios