ዘካርያስ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢየሩሳሌምን ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ ለመመለስ እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ 1 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2 “ለሕዝብዋ ስላለኝ ፍቅር ኢየሩሳሌምን መርዳት እፈልጋለሁ፤ በጠላቶችዋ ላይ እንድቈጣ ያደረገኝም ይኸው ስለ እርስዋ ያለኝ ፍቅር ነው። 3 እኔ እንድኖርባት ወደ ተቀደሰችው ከተማዬ ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ፤ የታመነች ከተማ በመሆን ትታወቃለች፤ እኔ የሠራዊት አምላክ የምኖርበት ተራራ፥ የተቀደሰ ተራራ ተብሎ ይጠራል፤ 4 ሰዎች ረጅም ዕድሜ ስለሚኖሩ ሽማግሌዎችና አሮጊቶች ምርኲዝ እየያዙ በመሄድ በኢየሩሳሌም አደባባዮች እንደገና ይቀመጣሉ፤ 5 መንገዶችዋም ሁሉ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንደገና የተሞሉ ይሆናሉ። 6 “በእነዚህ ቀኖች ከሕዝቡ ለተረፉት ይህ የማይቻል ነገር ቢመስልም እንኳ በውኑ ለእኔ የማይቻል ነገር አለን? 7 እኔ ሕዝቤን በስደት ከሚኖሩበት ከምሥራቅና ከምዕራብ አገር እታደጋቸዋለሁ፤ 8 መልሼ በማምጣት በኢየሩሳሌም እንዲኖሩ አደርጋቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም በእውነትና በጽድቅ አምላካቸው እሆናለሁ። 9 “ለሠራዊት አምላክ ቤተ መቅደስን እንደገና ለመሥራት መሠረት በተጣለበት በቅርብ ጊዜ የነበሩ ነቢያት የተናገሩትን ቃል የሰማችሁ እናንተ አይዞአችሁ በርቱ! 10 ከእነዚያ ቀኖች በፊት ለሰዎች የድካም ዋጋ ለእንስሶችም ኪራይ አይከፈልም ነበር፤ ሰውን ሁሉ በጐረቤቱ ላይ በጠላትነት እንዲነሣሣ ስላደረግሁ ማንም ሰው ሲወጣና ሲገባ ሰላም አልነበረውም። 11 አሁን ግን ከዚህ ሕዝብ የተረፉትን እንደ ቀድሞው ጊዜ አላደርግባቸውም። 12 እህላቸውን በሰላም ዘርተው ፍሬውን ይሰበስባሉ የወይን ተክሎቻቸውም ያፈራሉ። በቂ ዝናብ ስለሚዘንብ ምድሪቱ ብዙ ሰብል ትሰጣለች፤ ከስደት ለተረፉት ሕዝብ ይህን ሁሉ በረከት እሰጣለሁ። 13 በሕዝቦች ዘንድ እንደ ርግማን ትቈጠሩ የነበራችሁት እናንተ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝቦች ሆይ! እኔ አድናችኋለሁ፤ ለበረከትም ትሆናላችሁ፤ ስለዚህ አትፍሩ! በርቱ።” 14 “እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ባስቈጡኝ ጊዜ ባለመራራት ቅጣት ላመጣባችሁ ወሰንኩ። 15 ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ሕዝብ መልካምን ነገር ማድረግ ወስኜአለሁና አይዞአችሁ፤ አትፍሩ። 16 እናንተ ልታደርጉት የሚገባ ነገር ይህ ነው፦ እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በፍርድ ሸንጎዎቻችሁ ሰላም የሚገኝበትን እውነተኛ ፍርድ ስጡ። 17 እርስ በርሳችሁ ለመጐዳዳት አንዱ በሌላው ላይ ተንኰል አያስብ፤ በሐሰት አትማሉ፤ እኔ ይህን ሁሉ እጠላለሁ” ይላል እግዚአብሔር። 18 የሠራዊት አምላክ እንዲህ አለኝ፦ 19 “በአራተኛው፥ በአምስተኛው፥ በሰባተኛውና በዐሥረኛው ወር ትጠብቁት የነበረው ጾም ሁሉ ለይሁዳ ሕዝብ የተድላና የደስታ በዓል ይሆንላቸዋል፤ እናንተ ግን እውነትንና ሰላምን ውደዱ።” 20 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ሌሎች ሕዝቦችና በብዙ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም የሚጐርፉበት ጊዜ ይመጣል። 21 የአንድ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ከተማ ሄደው ‘ኑ! ከሠራዊት አምላክ ቸርነትን እንለምን፤ እኛም ወደዚያ መሄዳችን ነው!’ ይሉአቸዋል። 22 በዚህ ዐይነት ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ለመስገድና የእርሱንም በረከት ያገኙ ዘንድ ለመጸለይ ብዙ ሰዎችና ታላላቅ ሕዝቦች ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ። 23 በእነዚያ ቀኖች ዐሥር የሌላ አገር ሰዎች ወደ አንድ አይሁዳዊ ቀርበው የልብሱን ዘርፍ በመያዝ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለ ሰማን ከእናንተ ጋር እንሂድ’ ይሉታል።” |