ዘካርያስ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ትክክለኛ ያልሆነውን ጾም አይቀበለውም 1 ዳርዮስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ኪስሌው የተባለ ዘጠነኛው ወር በገባ በአራተኛው ቀን እግዚአብሔር ለዘካርያስ የነገረው ቃል ይህ ነው፤ 2 የቤትኤል ነዋሪዎች ሣርኤጼርንና ሬጌሜሌክን አብረዋቸው ከነበሩ ሰዎች ጋር ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ላኩአቸው፤ የላኩአቸውም የእግዚአብሔር በረከት ይወርድ ዘንድ እንዲጸልዩና፥ 3 የቤተ መቅደሱን ካህናትና ነቢያትን “እስከ አሁን ለብዙ ዓመቶች እንዳደረግነው በየአምስተኛው ወር በመጾም ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ ማዘናችንን እንቀጥልን?” ብለው እንዲጠይቁ ነበር። 4 ከዚህም በኋላ ወደ እኔ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ 5 ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉና ለካህናቱ እንዲህ በላቸው፦ “ባለፉት ሰባ ዓመቶች በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር የጾማችሁትና ያዘናችሁት እኔን ለማክበር ነበርን? 6 በምትበሉበትና በምትጠጡበትስ ጊዜ የምትበሉትና የምትጠጡት ለራሳችሁ ብቻ አልነበረምን?” 7 ኢየሩሳሌም በልጽጋና በሕዝብ ተሞልታ በነበረችበት ጊዜ፥ በከተማይቱ ዙሪያ ባሉ መንደሮች ብቻ ሳይሆን በደቡብ ክፍልና በምዕራብ ኰረብቶች ግርጌ ብዙ ሕዝብ በሚኖሩበት ዘመን እግዚአብሔር በቀድሞ ነቢያቱ አማካይነት የተናገረውም ይህንኑ ቃል ነበር። አለመታዘዝ የስደት ምክንያት መሆኑ 8 እግዚአብሔር ዘካርያስን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 9 “እኔ የሠራዊት አምላክ ለሕዝቤ የሰጠሁት ትእዛዝ ይህ ነበር፤ ‘በትክክል ፍረዱ፥ እርስ በርሳችሁም አንዳችሁ ለሌላው ምሕረትና ርኅራኄን አድርጉ፤ 10 በመካከላችሁ የሚኖሩትን ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች፥ አባትና እናት የሌላቸውን ድኻ አደጎች፥ መጻተኞችንና ችግረኞችን አትጨቊኑ፤ እርስ በርሳችሁ አንዳችሁ ሌላውን ለመጒዳት አታስቡ።’ 11 “እነርሱ ግን ላለማዳመጥ እልኸኞች ሆኑ፤ እንዳይሰሙም ጆሮአቸውን ደፈኑ። 12 ልባቸውንም እንደ አለት ድንጋይ አጠነከሩ፤ ጥንት በነበሩት ነቢያት አማካይነት እኔ የሠራዊት አምላክ በመንፈሴ የሰጠኋቸውን ሕግ ሁሉ በእልኸኛነት የማያዳምጡ ሆኑ፤ ስለዚህ እኔ የሠራዊት አምላክ ኀይለኛ ቊጣ አወረድኩባቸው። 13 እኔ ስናገር ‘አናዳምጥም’ ስላሉ፥ እነርሱም ወደ እኔ በጸለዩ ጊዜ መልስ አልሰጠኋቸውም ይላል የሠራዊት አምላክ። 14 እንደ ዐውሎ ነፋስ ጠራርጌ በመውሰድም በማያውቁት ባዕድ አገር እንዲኖሩ አደረግኋቸው፤ ይህችም መልካም ምድር ማንም የማይኖርባት ባድማ ሆና ቀረች፥ ያቺ ያማረች ምድርም ባድማ ሆነች።” |