Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘካርያስ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ነቢዩ ዘካርያስ ስለ መቅረዝ ያየው ራእይ

1 ያነጋግረኝ የነበረው መልአክ እንደገና መጥቶ ከእንቅልፉ እንደሚቀሰቀስ ሰው ቀሰቀሰኝ፤

2 “ይህ የምታየው ምንድን ነው?” ብሎም ጠየቀኝ። እኔም እንዲህ ብዬ መለስኩለት፦ “ሰባት መብራቶች ያሉበት አንድ የወርቅ መቅረዝ አያለሁ፤ በአናቱም ላይ የዘይት ማሰሮ አለ፤ ሰባቱም መብራቶች የክር ማስተላለፊያ ቧንቧ አላቸው።

3 በመቅረዙም አጠገብ ሁለት የወይራ ዛፎች በማሰሮው ግራና ቀኝ ይታያሉ፤”

4 እኔም ያነጋግረኝ የነበረውን መልአክ “ጌታዬ ሆይ! እነዚህ የምን ምሳሌዎች ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት።

5 እርሱም “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን?” አለኝ። እኔም “ጌታዬ ሆይ! አላውቅም” አልኩት።

6 ለዘሩባቤል እንዳስታወቀው መልአኩ የነገረኝ የሠራዊት አምላክ ቃል ይህ ነው፤ “ድል የምትነሣው በመንፈሴ እንጂ በኀይልና በብርታት አይደለም።

7 እንደ ተራራ በፊትህ የተደቀነው መሰናክል ሁሉ ይወገዳል፤ ቤተ መቅደሱንም መልሰህ ትሠራለህ፤ የመደምደሚያውንም ድንጋይ በስፍራው መልሰህ በምታኖርበት ጊዜ ሕዝቡ ‘እንዴት ውብ ነው! ውብ ነው!’ እያሉ የደስታ ድምፅ ያሰማሉ።”

8 እንደገናም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

9 “የዘሩባቤል እጆች የዚህን ቤተ መቅደስ መሠረት ጥለዋል፤ እጆቹም ይፈጽሙታል፤ ያን ጊዜ የሠራዊት አምላክ እኔን ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።

10 ትንሽ ነገር የሚደረግበትን ቀን የናቀ ቱምቢውን በዘሩባቤል እጅ ሲያይ ይደሰታል፤ እነዚህ ሰባቱ መቅረዞች ዓለምን የሚያካልሉ የእግዚአብሔር ዐይኖች ናቸው።”

11 እኔም እንዲህ በማለት መልሼ ጠየቅሁት፦ “እነዚህስ በመቅረዙ ግራና ቀኝ የቆሙት የወይራ ዛፎች የምን ምሳሌዎች ናቸው?

12 የወይራው ዘይት ከሚፈስስባቸው ከሁለቱ የወርቅ ቧንቧዎች አጠገብ ያሉትስ ሁለቱ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የምን ምሳሌዎች ናቸው?”

13 እርሱም “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን?” አለኝ፤ እኔም “ጌታዬ ሆይ! አላውቅም” አልኩት።

14 እርሱም “እነዚህ እግዚአብሔር የቀባቸውና በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ቆመው የሚያገለግሉ ሁለቱ ሰዎች ናቸው” አለኝ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios