Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘካርያስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ነቢዩ ዘካርያስ ስለ መለኪያ ገመድ ያየው ራእይ

1 በሌላም ራእይ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ አንድ ሰው አየሁ፤

2 እኔም “ወዴት እየሄድክ ነው?” ብዬ ጠየቅሁት፤ እርሱም “የኢየሩሳሌም ርዝመትና ስፋት ምን ያኽል እንደ ሆነ ለመለካት መሄዴ ነው” አለኝ።

3 ከዚህ በኋላ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወደፊት ሲራመድና ሌላ መልአክም ሊገናኘው ሲመጣ አየሁ።

4 የመጀመሪያው መልአክ ሁለተኛውን እንዲህ አለው፦ “የመለኪያ ገመድ ወደያዘው ወጣት በሩጫ ሂድና ‘በኢየሩሳሌም ብዙ ሕዝብና ብዙ እንስሶች ስለሚገኙ ትልቅ ግንብ መሥራት ያዳግታል’ ብለህ ንገረው።

5 እግዚአብሔር ራሱ በዙሪያዋ እንደ እሳት ቅጽር ሆኖ ከተማይቱን እንደሚጠብቅና በክብሩም በዚያ እንደሚኖር ተስፋ ሰጥቶአል።”


ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለስደተኞች የተደረገ ጥሪ

6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በየአራቱም ማእዘን በትኜአችሁ ነበር፤ አሁን ግን ከሰሜን ምድር ተነሥታችሁ ሽሹ።

7 በባቢሎን የምትኖሩ እናንተ ስደተኞች ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።”

8 እናንተን የሚነካ የእርሱን ዓይን ብሌን እንደሚነካ ሆኖ ይቈጠራል። የክብር ጌታ በበዘበዙአችሁ ሕዝቦች ላይ በላከኝ ጊዜ የተናገራቸው ቃላት እነዚህ ናቸው።

9 “አሁን እኔ በእነርሱ ላይ እጄን አነሣለሁ፤ እነርሱም ባሪያዎች አድርገው ለገዙአቸው ምርኮኞች ይሆናሉ፤ ከዚያ በኋላ እናንተም የሠራዊት አምላክ እኔን እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።

10 “እኔ መጥቼ በመካከላችሁ ስለምኖር የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! ዘምሩ! ደስም ይበላችሁ!” ይላል እግዚአብሔር።

11 በዚያን ጊዜ ብዙ የአሕዛብ ነገዶች ከእግዚአብሔር ጋር ተባብረው ወገኖቹ ይሆናሉ። እርሱም በመካከላችሁ ይኖራል፤ እኔንም ወደ እናንተ የላከኝ እርሱ መሆኑን ትገነዘባላችሁ።

12 በተቀደሰችው ምድር ይሁዳን የራሱ ርስት ያደርጋታል፤ ኢየሩሳሌምንም እንደገና ይመርጣታል።

13 እግዚአብሔር ከተቀደሰ መኖሪያው ለመምጣት ስለ ተነሣ ሁላችሁም በፊቱ ዝም በሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios