ዘካርያስ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ወደ እርሱ እንዲመለሱ ሕዝቡን መጥራቱ 1 ዳርዮስ የፋርስ ንጉሥ በሆነ በሁለተኛው ዓመት፥ በስምንተኛው ወር እግዚአብሔር በዒዶ የልጅ ልጅ በበራክዩ ልጅ በነቢዩ በዘካርያስ አማካይነት የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ 2 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘካርያስን ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ተናገር አለው፦ “እኔ እግዚአብሔር በቀድሞ አባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቼ ነበር፤ 3 አሁን ግን እናንተን የምላችሁ ይህ ነው፦ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ። 4 እንደ ቀድሞ አባቶቻችሁ አትሁኑ፤ እነርሱን የቀድሞ ነቢያት ‘ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ’ ብለው አስጠንቅቀዋቸው ነበር፤ አባቶቻችሁ ግን ቃሌን አላደመጡም፤ ትእዛዜንም አልጠበቁም። 5 የቀድሞ አባቶቻችሁ አሁን የት አሉ? ነቢያቱስ ለዘለዓለም ይኖራሉን? 6 ነገር ግን አገልጋዮቼ በሆኑት በነቢያት አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻችሁ ያስተላለፍኩትን ሕግና ትእዛዝ ባለመጠበቃቸው ተቀጥተው የለምን? ስለዚህ በበደላቸው ተጸጸተው ‘የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ባቀደው መሠረት እንደ ሥራችንና እንደ አካሄዳችን በእኛ ላይ ቅጣትን ማምጣቱ ትክክለኛ ነው’ አሉ።” ነቢዩ ዘካርያስ ስለ ፈረሶች ያየው ራእይ 7 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ ሼባጥ የተባለው ዐሥራ አንደኛው ወር በገባ በሃያ አራተኛው ቀን፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ የዒዶ የልጅ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ መጣ። 8 የእግዚአብሔር መልአክ በቀይ ፈረስ ላይ ተቀምጦ አየሁ። እርሱም በሸለቆው ውስጥ ባሉ በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆመ፤ በስተኋላውም ቀይ፥ ሐመርና አምባላይ ፈረሶች ይከተሉት ነበር። 9 እኔም “ጌታዬ ሆይ! እነዚህ ፈረሶች የምን ምሳሌ ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት። እርሱም “የእነዚህ ፈረሶች ምሳሌነት ምን እንደ ሆነ አሳይሃለሁ፤ 10 ምድርን ተዘዋውረው ይቃኙ ዘንድ እግዚአብሔር የላካቸው ናቸው” አለኝ። 11 እነርሱም “ምድርን ሁሉ ዞረን መረመርን፤ ምድሪቱ በመላ ሰላም ነች” ብለው ለመልአኩ ነገሩት። 12 መልአኩም “የሠራዊት አምላክ ሆይ! ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ሁሉ ከተቈጣህ እነሆ ሰባ ዓመቶች አለፉ፤ ምሕረት የማታደርግላቸው እስከ መቼ ነው?” ሲል ጠየቀ። 13 ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል መልስ ሰጠው። 14 ስለዚህም መልአኩ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለውን ቃል እንዲህ ብለህ ዐውጅ አለኝ፥ “እኔ ለተቀደሰችው ከተማዬ ለኢየሩሳሌም ታላቅ ፍቅርና ብርቱ ቅናት አለኝ፤ 15 ሰላም አግኝተው በጸጥታ በሚኖሩ በአሕዛብ መንግሥታት ላይ እጅግ ተቈጥቼአለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ሕዝቤን ከመቅጣት መለስ ባልኩበት ጊዜ እነዚያ የአሕዛብ መንግሥታት ሕዝቤን ከተጠበቀው በላይ አሠቃይተዋል። 16 ስለዚህ ለከተማይቱ ምሕረትን ለማሳየት ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ ቤተ መቅደሴና ከተማይቱ እንደገና ታድሰው ይሠራሉ።” 17 መልአኩም እንደገና “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከተሞቹ ተመልሰው እንደሚበለጽጉና ኢየሩሳሌምንም እንደ ጥንቱ እንደሚረዳ የራሱ ከተማም እንደሚያደርጋት ተናገር” አለኝ። ነቢዩ ዘካርያስ ስለ አራቱ የበሬ ቀንዶች ያየው ራእይ 18 በሌላም ራእይ አራት የበሬ ቀንዶችን አየሁ፤ 19 ያነጋግረኝ የነበረውንም መልአክ “እነዚህ ቀንዶች የምን ምሳሌ እንደ ሆኑ ንገረኝ” አልኩት። እርሱም “እነርሱ የይሁዳ፥ የእስራኤልና የኢየሩሳሌም ሕዝቦች እንዲበተኑ ያደረጉ መንግሥታት ናቸው” አለኝ። 20 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር መዶሻ የያዙ አራት አንጥረኞችን አሳየኝ፤ 21 እኔም “እነዚህ ሰዎች የመጡት ምን ሊሠሩ ነው?” ብዬ ጠየቅሁት፤ እርሱም “እነርሱ የመጡት የይሁዳን ምድር ፈጽሞ አጥፍተው፥ ሕዝብዋ ተበታትኖ እንዲቀር ያደረጉትን የአሕዛብ መንግሥታት ለማሸበርና ለመጣል ነው” አለኝ። |