Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሮሜ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት

1 ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖሩ አሁን ኲነኔ የለባቸውም።

2 በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘውን ሕይወት የሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቶኛል።

3 ከሰው ባሕርይ ደካማነት የተነሣ ሕግ ሊያደርገው ያልቻለውን እግዚአብሔር አድርጎታል፤ የገዛ ልጁንም በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌነት በኃጢአት ምክንያት ልኮ በሥጋው ኃጢአትን በፍርድ አስወገደ።

4 ይህንንም ያደረገው በሥጋ ፈቃድ ሳይሆን በመንፈስ ፈቃድ በምንመላለስ በእኛ ትክክለኛው የሕግ ትእዛዝ እንዲፈጸም ነው።

5 በሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሥጋዊ ነገርን፥ በመንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን መንፈሳዊ ነገርን ያስባሉ።

6 ሥጋዊ ነገርን ማሰብ ሞትን ያመጣል፤ መንፈሳዊ ነገርን ማሰብ ግን ሕይወትንና ሰላምን ይሰጣል።

7 ሥጋዊ ነገርን የሚያስብ ሰው ለእግዚአብሔር ሕግ ስለማይታዘዝና መታዘዝም ስለማይችል የእግዚአብሔር ጠላት ነው።

8 ለሥጋዊ ነገር የሚገዙ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም።

9 እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ በመንፈስ ፈቃድ እንጂ በሥጋ ፈቃድ አትኖሩም፤ የክርስቶስ መንፈስ የሌለውም ሰው የክርስቶስ ወገን አይደለም።

10 ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ከሆነ ምንም እንኳ ሥጋችሁ በኃጢአት ምክንያት የሚሞት ቢሆን እግዚአብሔር ስላጸደቃችሁ መንፈሳችሁ ሕያው ነው።

11 ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት ያስነሣው አምላክ በውስጣችሁ በሚኖረው መንፈሱ አማካይነት ለሟች ሥጋችሁ ሕይወትን ይሰጠዋል።

12 ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ! በሕይወታችን ግዴታ አለብን፤ ነገር ግን ይህ ግዴታ በሥጋ ፈቃድ ለመኖር አይደለም።

13 በሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ሥጋዊ ሥራችሁን ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።

14 በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።

15 ስለዚህ “አባ! አባታችን ሆይ!” ብላችሁ የምትጠሩበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ በፍርሃት ለመኖር እንደገና የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁም።

16 የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኛ መንፈስ ጋር ሆኖ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለእኛ ይመሰክራል።

17 እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን የእርሱ ወራሾች ነን፤ ከክርስቶስም ጋር እንወርሳለን፤ አሁን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች ብንሆን በኋላ የክብሩ ተካፋዮች እንሆናለን።


የሚመጣው ክብር

18 የአሁኑ ጊዜ መከራ ወደፊት ለእኛ ከሚገለጥልን ክብር ጋር ቢመዛዘን በምንም ሊተካከል እንደማይችል አድርጌ እቈጥረዋለሁ።

19 ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃል።

20 ፍጥረት ሁሉ ከንቱ እንዲሆን ተፈርዶበታል፤ ይኸውም በራሱ ፍላጎት ሳይሆን በተስፋ እንዲጠባበቅ ባደረገው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።

21 ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ከጥፋት ባርነት ነጻ ወጥቶ ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር የነፃነትና የክብር ተካፋይ እንደሚሆን ነው።

22 ፍጥረት ሁሉ በአንድ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በምጥ ጭንቀት ተይዞ በመቃተት ላይ መኖሩን እናውቃለን።

23 ነገር ግን በመቃተት ላይ ያለው ፍጥረት ብቻ አይደለም፤ የመጀመሪያውን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ የተቀበልን እኛም የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን የእግዚአብሔር ልጆች መሆንን በተስፋ እየተጠባበቅን በውስጣዊ ሰውነታችን በመቃተት ላይ እንገኛለን፤

24 እኛ የዳንነው በዚሁ ተስፋ ነው። ነገር ግን ተስፋ የምናደርገው ነገር የሚታይ ከሆነ ተስፋ መሆኑ ይቀራል፤ የሚታየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?

25 የማናየውን ነገር ተስፋ ካደረግን ግን በትዕግሥት እንጠባበቃለን።

26 እንዲሁም እንዴት መጸለይ እንደሚገባን ስለማናውቅ መንፈስ ቅዱስ በድካማችን ይረዳናል፤ በቃል ሊገለጥ በማይቻል መቃተት ያማልደናል።

27 የሰውን ልብ የሚመረምር አምላክ የመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፤ መንፈስ ቅዱስ ስለ ምእመናን የሚያማልደው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነው።

28 እግዚአብሔርን ለሚወዱና እንደ ፈቃዱም ለተጠሩት ሰዎች እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ለበጎ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን።

29 ይህም የሆነበት ምክንያት አስቀድሞ ያወቃቸው ልጁን እንዲመስሉና ልጁም ከብዙ ወንድሞች መካከል በኵር እንዲሆን እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ወሰነ ነው።

30 አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውንም አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም አከበራቸው።


የእግዚአብሔር ፍቅር

31 እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል?

32 እግዚአብሔር ለአንድ ልጁ ሳይራራ ስለ እኛ አሳልፎ ከሰጠው እንዴት ከልጁ ጋር ሁሉን ነገር በነጻ አይሰጠንም?

33 እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቃቸው እርሱ ነው።

34 ማነው የሚፈርድ? ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈርድባቸዋልን? እርሱ ስለ እኛ የሞተ፥ ከሞት ተነሥቶ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የተቀመጠ፥ ስለ እኛም የሚማልድ ነው።

35 ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል ማነው? ችግር ወይስ መከራ? ስደት፥ ወይስ ራብ? ወይስ ራቊትነት፥ ወይስ አደጋ? ወይስ ሰይፍ?

36 ይህም፥ “ስለ አንተ በየቀኑ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጠርን” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

37 እንግዲህ በወደደን በክርስቶስ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ድል በመንሣት ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።

38 ስለዚህ ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ባለሥልጣኖችም ቢሆኑ፥ አሁን ያለውም ቢሆን፥ በኋላ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኀይሎችም ቢሆኑ፥

39 ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካገኘነው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios