Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሮሜ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ከሕግ ነጻ ስለ መሆን

1 ወንድሞቼ ሆይ! ይህን አታውቁምን? የምናገረው ሕግን ለሚያውቁ ሰዎች ነው፤ ሕግ በሰው ላይ ሥልጣን የሚኖረው ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ብቻ ነው።

2 ለምሳሌ፥ ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት እስካለ ድረስ ከእርሱ ጋር በሕግ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ከሞተ ግን ከታሰረችበት ሕግ ነጻ ናት።

3 ስለዚህ ባልዋ በሕይወት እያለ ሌላ ወንድ ብታገባ አመንዝራ ትባላለች። ባልዋ ከሞተ ግን ከእርሱ ጋር ከታሰረችበት ሕግ ነጻ ትወጣለች፤ ሌላ ወንድ ብታገባም አመንዝራ አይደለችም።

4 ወንድሞቼ ሆይ፥ የእናንተም ሁኔታ እንደዚሁ ነው፤ እናንተ የክርስቶስ አካል ክፍል ስለ ሆናችሁ በሞት የመለየትን ያኽል ከሕግ ተለይታችኋል፤ ስለዚህ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ፍሬ እንድናፈራ ከሞት የተነሣው የክርስቶስ ወገኖች ሆናችኋል።

5 በሥጋ ፈቃድ እንመላለስ በነበረበት ጊዜ በሕግ የሚነሣሣው ክፉ ምኞት ለሞት ፍሬ እንድናፈራ በሰውነታችን ክፍሎች ውስጥ ይሠራ ነበር።

6 አሁን ግን አስሮን ከነበረው ሕግ በሞት የመለየት ያኽል ስለ ተለየን ከሕግ እስራት ነጻ ወጥተናል፤ ስለዚህ ከእንግዲህ የምናገለግለው በአዲሱ መንፈሳዊ መመሪያ እንጂ አስቀድሞ በተጻፈው በአሮጌው የሕግ መመሪያ አይደለም።


ሕግና ኃጢአት

7 እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ራሱ ኃጢአት ነውን? አይደለም! ነገር ግን ኃጢአት ምን መሆኑን እንዳውቅ ያደረገኝ ሕግ ነው። ሕግ “አትመኝ” ባይል ኖሮ ምኞት ምን መሆኑን ባላወቅሁም ነበር።

8 ኃጢአት ከሕግ በመጣው ትእዛዝ ዕድል አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በኔ ውስጥ እንዲቀሰቀስ አደረገ። ሕግ ከሌለ ግን ኃጢአት የሞተ ነገር ነው።

9 ቀድሞ ሕግ ባልነበረበት ጊዜ እኔ በሕይወት እኖር ነበር፤ የሕግ ትእዛዝ በመጣ ጊዜ ግን እኔ ሞቼ ኃጢአት ሕይወት አገኘ።

10 ለሕይወትም የተሰጠው የሕግ ትእዛዝ በእኔ ላይ ሞትን አመጣብኝ።

11 ኃጢአት የሕግን ትእዛዝ ሰበብ አድርጎ አታለለኝ፤ በትእዛዝም አማካይነት ገደለኝ።

12 ስለዚህ ሕግ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዝም ቅዱስና እውነት መልካምም ነው።

13 ታዲያ፥ ይህ መልካም የሆነው ነገር በእኔ ሞትን አመጣብኝ ማለት ነውን? አይደለም! ነገር ግን ኃጢአት፥ ኃጢአት ሆኖ እንዲገለጥ በመልካሙ ነገር አማካይነት ሞትን አመጣብኝ፤ ስለዚህ ኃጢአት በትእዛዝ አማካይነት የበለጠ ኃጢአተኛ ሆነ።


በሰው ሕይወት ውስጥ ያለ ትግል

14 ሕግ መንፈሳዊ መሆኑን እናውቃለን። እኔ ግን የኃጢአት ባሪያ ለመሆን የተሸጥሁ ሥጋዊ ነኝ።

15 እኔ የማደርገውን አላውቅም፤ የምወደውን ነገር ማድረግ ትቼ የምጠላውን ነገር አደርጋለሁ።

16 እንግዲህ እኔ የማደርገው የማልፈልገውን ነገር ከሆነ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።

17 ማድረግ የማልፈልገውን ነገር የሚያደርገው በእኔ ውስጥ ያለው ኃጢአት ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።

18 በእኔ ወይም በእኔ ሥጋዊ ባሕርይ ምንም መልካም ነገር እንደሌለ ዐውቃለሁ፤ መልካም ነገርን የማድረግ ፍላጎት ቢኖረኝም እንኳ ያን መልካም ነገር ለማድረግ ችሎታ የለኝም።

19 ማድረግ የምፈልገውን መልካም ነገርን አላደርግም፤ ዳሩ ግን የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁ።

20 ማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር የማደርግ ከሆንኩ ይህን የሚያደርገው በእኔ ውስጥ ያለው ኃጢአት ነው እንጂ እኔ አይደለሁም ማለት ነው።

21 ስለዚህ ሕግ በሥራ ላይ ውሎ አያለሁ፤ መልካም ነገርን ማድረግ ስፈልግ ክፉ ነገርን ለማድረግ እገደዳለሁ።

22 ውስጣዊ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል።

23 ይሁን እንጂ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር እየተቃረነ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ ለሚሠራው የኃጢአት ሕግ እስረኛ የሚያደርገኝ ሌላ የተፈጥሮ ዝንባሌ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ መኖሩን አያለሁ።

24 እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ሟች ሰውነትስ ማን ያድነኛል?

25 በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሚያድነኝ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እንግዲህ እኔ በአእምሮዬ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ ተገዢ ስሆን በሥጋ ባሕርዬ ለኃጢአት ሕግ ተገዢ ሆኜአለሁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios