Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሮሜ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ከኃጢአት ተለይቶ በክርስቶስ መኖር

1 እንግዲህ ምን እንላለን? የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን?

2 አይደለም! እኛ በሞት የመለየትን ያኽል ከኃጢአት የተለየን ሆነን ሳለ እንዴት በኃጢአት ጸንተን እንኖራለን?

3 ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ለመሆን የተጠመቅን ሁሉ የሞቱም ተካፋዮች ለመሆን መጠመቃችንን አታውቁምን?

4 በጥምቀት ከእርሱ ጋር በተቀበርን ጊዜ የእርሱም ሞት ተካፋዮች ሆነናል፤ ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደ ተነሣ እኛም በአዲስ ሕይወት እንኖራለን።

5 በሞቱ ከእርሱ ጋር እንዲህ አንድ ከሆንን እንዲሁ በትንሣኤው ከእርሱ ጋር አንድ እንሆናለን።

6 ኃጢአተኛው ሰውነታችን እንዲወገድና የኃጢአት ባሪያዎች መሆናችን እንዲቀር አሮጌው ሰውነታችን ከክርስቶስ ጋር መሰቀሉን እናውቃለን።

7 የሞተ ሰው ለኃጢአት ከመገዛት ነጻ ነው።

8 እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር በሕይወት እንደምንኖር እናምናለን፤

9 ክርስቶስ ከሞት በመነሣቱ ምክንያት ዳግመኛ እንደማይሞትና ሞትም በእርሱ ላይ ሥልጣን እንደሌለው እናውቃለን።

10 እርሱ በሞተ ጊዜ ኃጢአት በእርሱ ላይ ሥልጣን እንዳይኖረው በማያዳግም ሁኔታ አንድ ጊዜ ሞቶአል፤ አሁንም በሕይወት ሲኖር ለእግዚአብሔር ይኖራል።

11 እንግዲህ እናንተ የመሞት ያኽል ከኃጢአት እንደ ተለያችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ግን ለእግዚአብሔር በሕይወት እንደምትኖሩ አስቡ።

12 ስለዚህ ኃጢአት በሚሞተው ሰውነታችሁ ላይ ሥልጣን እንዲኖረውና ለሥጋ ምኞትም ተገዢ እንዲያደርጋችሁ አትፍቀዱለት።

13 እንዲሁም የሰውነታችሁን ክፍሎች የዐመፅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታስገዙ፤ ነገር ግን ከሞት ተነሥታችሁ ሕያዋን እንደ ሆናችሁ በማድረግ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የሰውነታችሁንም ክፍሎች ሁሉ የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አስገዙ።

14 አሁን እናንተ የምትኖሩት ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆነ ኃጢአት ሊገዛችሁ አይገባም።


የጽድቅ አገልጋዮች መሆን

15 እንግዲህ ምን እንላለን? ከሕግ በታች መሆናችን ቀርቶ ከጸጋ በታች ስለ ሆንን ኃጢአት እንሥራ ማለት ነውን? ከቶ አይደለም!

16 ለአንድ ሰው አገልጋዮች ሆናችሁ ለመታዘዝ ራሳችሁን ስታቀርቡ ለዚያ ለምትታዘዙለት ሰው አገልጋዮች መሆናችሁን ታውቃላችሁ፤ እንዲሁም ለኃጢአት ብትታዘዙ ሞትን ለሚያመጣባችሁ ኃጢአት አገልጋዮች ትሆናላችሁ፤ ለእግዚአብሔር ብትታዘዙ ግን ጽድቅን ታገኛላችሁ።

17 እናንተ አስቀድሞ የኃጢአት ባሪያዎች ነበራችሁ፤ አሁን ግን ለተቀበላችሁት ትምህርት ከልብ በመታዘዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።

18 ከኃጢአት ባርነት ነጻ ወጥታችሁ የጽድቅ አገልጋዮች ሆናችኋል።

19 እኔ እንዲህ ለሰው በሚገባ ቋንቋ የምናገረው ከአስተሳሰባችሁ ደካማነት የተነሣ ነው። አስቀድሞ የሰውነት ክፍሎቻችሁን የርኲሰትና የዐመፅ አገልጋዮች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ ሁሉ እንዲሁም አሁን የሰውነት ክፍሎቻችሁ እንዲቀደሱ የጽድቅ አገልጋዮች አድርጋችሁ አቅርቡ።

20 የኃጢአት ባሪያዎች በነበራችሁበት ጊዜ ጽድቅ የማድረግ ግዴታ አይሰማችሁም ነበር።

21 ታዲያ፥ በዚያን ጊዜ ምን ጥቅም አገኛችሁ? አሁን ከሚያሳፍራችሁ ነገር በቀር ምንም ጥቅም አላገኛችሁም፤ የዚህም ነገር መጨረሻ ሞት ነው።

22 አሁን ግን ከኃጢአት ባርነት ነጻ ወጥታችሁ የእግዚአብሔር አገልጋዮች በመሆናችሁ ቅድስናን ታገኛላችሁ፤ የቅድስናም መጨረሻ የዘለዓለም ሕይወት ነው።

23 ከኃጢአት የሚገኘው ዋጋ ሞት ነው፤ ከእግዚአብሔር የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የሚገኘው የዘለዓለም ሕይወት ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios