ሮሜ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምአብርሃም በእምነት መጽደቁ 1 እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም አገኘ የምንለው ምንድን ነው? 2 አብርሃም የጸደቀው በሥራ ቢሆን ኖሮ፥ የሚመካበት ነገር ባገኘ ነበር፤ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ፊት መመካት አይችልም። 3 ቅዱስ መጽሐፍ “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” ይላል። 4 የሚሠራ ሰው የሚያገኘው ደመወዝ ተገቢ የጒልበቱን ዋጋ ነው እንጂ ስጦታ አይደለም። 5 ሰው መልካም ሥራ ባይኖረው እንኳ ኃጢአተኞችን በሚያጸድቅ አምላክ ካመነ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቈጠርለታል። 6 ዳዊትም በበኩሉ እግዚአብሔር ያለ መልካም ሥራ የሚያጸድቀው ሰው ምን ያኽል የተባረከ መሆኑን ሲገልጥ እንዲህ ብሎአል፦ 7 “በደላቸው ይቅር የተባለላቸውና ኃጢአታቸው የተደመሰሰላቸው ሰዎች የተባረኩ ናቸው! 8 ጌታ ኃጢአቱን የማይቈጥርበት ሰው የተባረከ ነው!” 9 ታዲያ፥ ዳዊት የተናገረው ይህ በረከት ለተገረዙት ብቻ ነውን? ወይስ ላልተገረዙትም? ላልተገረዙትም ነው፤ “አብርሃም በእግዚአብሔር ስላመነ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” ብለናል። 10 እንግዲህ አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ የተቈጠረለት መቼ ነው? ከመገረዙ በፊት ነውን ወይስ ከተገረዘ በኋላ? ከመገረዙ በፊት ነው እንጂ ከተገረዘ በኋላ አይደለም። 11 አብርሃም ገና ከመገረዙ በፊት እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንደ ተቈጠረለት ማረጋገጫ ምልክት እንዲሆነው ተገረዘ፤ ስለዚህ አብርሃም፥ ሳይገረዙ ለሚያምኑና እምነታቸው ጽድቅ ሆኖ ለሚቈጠርላቸው ሁሉ አባት ነው። 12 እንዲሁም አብርሃም ለተገረዙትም አባት ነው፤ ለተገረዙት አባት የሆነበትም ምክንያት በመገረዛቸው ብቻ ሳይሆን እርሱ ከመገረዙ በፊት የነበረውን እምነት በመከተላቸውም ጭምር ነው። ስለ እምነት የተሰጠ ተስፋ 13 ለአብርሃምና ለዘሩ ዓለምን እንደሚወርስ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠው በእምነት ስላገኘው ጽድቅ ነው እንጂ ሕግን በመፈጸሙ አይደለም። 14 የተስፋው ወራሾች ሕግን የሚፈጽሙ ሰዎች ከሆኑማ እምነት ዋጋ አይኖረውም፤ ተስፋም ከንቱ መሆኑ ነው። 15 ሕግ የሚያመጣው የእግዚአብሔርን ቊጣ ነው፤ ሕግ ከሌለ ግን ሕግን የመተላለፍ በደል አይኖርም። 16 ስለዚህ ተስፋው የተመሠረተው በእምነት ላይ ነበር፤ ይህም ተስፋ ለአብርሃም ዘሮች ሁሉ ከእግዚአብሔር በጸጋ የተሰጠ መሆኑ በዚህ ተረጋግጦአል። ይህም ሕግን ለሚከተሉት ሰዎች ብቻ ሳይሆን እንደ አብርሃም ላመኑ ሁሉ ነው፤ በዚህም መሠረት አብርሃም የሁላችንም አባት ነውና። 17 ስለ አብርሃም፦ “የብዙ ሕዝብ አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ ተጽፎአል፤ ይህም ተስፋ ለአብርሃም የተሰጠው እርሱ የሞቱትን በሚያስነሣውና የሌለውን እንዲኖር በሚያደርገው አምላክ ስለ አመነ ነበር። 18 አብርሃም ዘርህ እጅግ ይበዛል ተብሎ በተነገረው መሠረት የብዙ ሕዝብ አባት እንደሚሆን ያመነውና ተስፋ ያደረገው ምንም ተስፋ በማይጣልበት ነገር ነው። 19 ዕድሜው መቶ ዓመት ያኽል ስለ ነበረ በሥጋው መድከም እንደ ሞተ በመሆን ምክንያት መውለድ እንደማይችልና ሣራም መኻንና ያረጀች በመሆንዋ መውለድ እንደማትችል ቢያውቅም በእምነቱ ደካማ አልሆነም። 20 በእምነቱ ብርቱ ሆኖ ለእግዚአብሔር ክብር ሰጠ እንጂ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ ባለማመን ከቶ አልተጠራጠረም። 21 እግዚአብሔር የሰጠውንም ተስፋ የሚፈጽም መሆኑን በሙሉ ልብ ያምን ነበር። 22 ስለዚህ ነው ለአብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ የተቈጠረለት። 23 ነገር ግን “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው ቃል የተጻፈው ለአብርሃም ብቻ ሳይሆን 24 ለእኛም ጭምር ነው፤ ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ባስነሣው አምላክ ለምናምን ለእኛም እምነታችን ጽድቅ ሆኖ ይቈጠርልናል። 25 ይህ ጌታችን ኢየሱስም ስለ ኃጢአታችን ለሞት ተላልፎ የተሰጠውና እኛንም ለማጽደቅ ከሞት የተነሣው ነው። |