ሮሜ 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሰላምታ 1 ፌቤ በክንክሪያ ከተማ ቤተ ክርስቲያንን የምታገለግል ታማኝ እኅታችን መሆንዋን እንድታውቁ እወዳለሁ። 2 እርስዋ እኔንና ሌሎችንም ብዙ ሰዎች የረዳች ስለ ሆነች ምእመናን እንግዶችን መቀበል እንደሚገባቸው ዐይነት በጌታ ስም ተቀብላችሁ በሚያስፈልጋት ነገር ሁሉ እንድትረዱአት ዐደራ እላችኋለሁ። 3 በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ተባባሪዎቼ ለሆኑት ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ 4 እነርሱ በእኔ ምትክ ለመሞት እንኳ የተዘጋጁ ነበሩ፤ በዚህም ዘወትር አመሰግናቸዋለሁ፤ እኔም ብቻ ሳልሆን ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የተመለሱ ምእመናን አብያተ ክርስቲያን ጭምር ያመሰግኑአቸዋል። 5 በእነርሱ ቤት ለጸሎት ለሚሰበሰቡት ምእመናንም ሰላምታ አቅርቡልኝ። በእስያ ክፍለ ሀገር በመጀመሪያ በክርስቶስ ላመነውና ለምወደው ለኤጴኔጦስ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 6 ለእናንተ ብዙ ለደከመችው ለማርያም ሰላምታ አቅርቡልኝ። 7 ከእኔ ጋር ታስረው ለነበሩና በሐዋርያትም መካከል ታዋቂዎች ለነበሩት አይሁድ ዘመዶቼ፥ ለአንድሮኒቆስና ለዩኒያስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እነርሱ በክርስቶስ በማመን እኔን ይቀድሙኛል። 8 በጌታ ለምወደው ለአምጵልያቶስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ 9 በክርስቶስ ሥራ ተባባሪያችን ለሆነው ለዑርባኖስና ለምወደውም ለእስጣኩስ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 10 በክርስቶስ መሆኑ ተፈትኖ ለተመሰከረለት ለአጴሊስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ ከአርስጦቡሎስ ቤተሰብ ለሆኑትም ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ 11 ለአይሁዳዊው ዘመዴ ለሄሮድዮን ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ ከናርሲሰስ ቤተ ሰዎች በጌታ ላመኑት ሰላምታ አቅርቡልኝ። 12 በጌታ አገልግሎት ለሚደክሙት ለትሩፋይናና ለትሩፎሳ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በጌታ አገልግሎት እጅግ ለደከመችውና በክርስቶስ ለምወዳት ለፔርሲስ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 13 ጌታን በማገልገል በጣም ለታወቀው ለሩፎስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እኔን እንደ ልጅዋ ትወደኝ ለነበረችው ለእናቱም ሰላምታ አቅርቡልኝ። 14 ለአስንክሪቶስና ለፍሌጎን፥ ለሄርሜስም፥ ለፓትሮባስም፥ ለሄርማስም፥ ከእነርሱም ጋር ላሉ ወንድሞች ሰላምታ አቅርቡልኝ። 15 ለፊሎሎጎስ፥ ለዩልያ፥ ለኔርያና ለእኅቱም ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እንዲሁም ለኦሉምፓስና ከእነርሱም ጋር ላሉ ምእመናን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 16 በተቀደሰ መሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የመጨረሻ ምክር 17 ወንድሞች ሆይ! ለተቀበላችሁት ትምህርት ተቃዋሚዎች በመሆን በመካከላችሁ መከፋፈልንና ችግርን ከሚያመጡ ሰዎች ተጠንቀቁ፤ ከእነርሱም ራቁ! 18 እንደእነዚህ ዐይነቶቹ ሰዎች ራሳቸውን እንጂ ጌታችንን ክርስቶስን አያገለግሉም። በለዘቡና በሚያቈላምጡ ቃላት የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ። 19 ለወንጌል ቃል ታዛዦች መሆናችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ ስለ ታወቀ ደስ ያለኝ ቢሆንም፥ ነገር ግን ለመልካም ነገር ጥበበኞች ለክፉ ነገር ግን የዋሆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። 20 ይህን ብታደርጉ የሰላም አምላክ ፈጥኖ ሰይጣንን በእግራችሁ ሥር ይቀጠቅጥላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። 21 የሥራ ተባባሪዬ ጢሞቴዎስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ እንዲሁም አይሁድ ዘመዶቼ የሆኑት ሉቂዮስና ኢያሶን ሶሲጳጥሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 22 ይህን መልእክት የጻፍኩ እኔም ጠርጥዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። 23 እኔንና በዚህ ያለውን መላ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተናግደው ጋይዮስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ የከተማይቱ በጅሮንድ የሆነው ኤራስጦስ፥ ወንድማችንም ቋርጦስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። [ 24 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን! አሜን።] የምስጋና ጸሎት 25 እኔ በማበሥረው የምሥራች ቃል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚተላለፈው መልእክትና ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተደብቆ በቈየው፥ አሁን ግን በተገለጠው የእውነት ምሥጢር አማካይነት እርሱ በእምነታችሁ እንድትቆሙ ሊያደርጋችሁ ይችላል። 26 አሁን ግን ይህ እውነት ተገልጦአል፤ በዘለዓለማዊው አምላክ ትእዛዝ ሁሉም አምነው እንዲታዘዙ በነቢያት መጻሕፍት አማካይነት ሕዝቦች ሁሉ እንዲያውቁት ተደርጓል። 27 እርሱ ብቻ ጥበብ ላለው ለአንድ አምላክ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ምስጋና ይሁን! አሜን። |