ሮሜ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሆነው፥ ለሐዋርያነት ከተጠራው፥ የእግዚአብሔርንም ወንጌል ለማስተማር ከተመረጠው ከጳውሎስ የተላከ። 2 ይህም ወንጌል እግዚአብሔር በነቢያት አማካይነት በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ የሰጠው የተስፋ ቃል ነው። 3 ወንጌሉ የእግዚአብሔር ልጅ በሰብአዊነቱ በኩል፥ ከዳዊት ዘር መወለዱን የሚያበሥር ነው፤ 4 እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስናው መንፈስ ከሞት በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በታላቅ ኀይል ታወቀ። 5 ስለ ክርስቶስ ስም አሕዛብ ሁሉ እንዲያምኑና እንዲታዘዙ ለማድረግ በእርሱ አማካይነት ለሐዋርያነት የሚያበቃንን ጸጋ ተቀብለናል። 6 እናንተም የኢየሱስ ክርስቶስ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ከጠራቸው ወገኖች መካከል ናችሁ። 7 ስለዚህ በሮም ለምትኖሩ፥ እግዚአብሔር ለወደዳችሁና ወገኖቹ እንድትሆኑ ለጠራችሁ ሁሉ፦ ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። የምስጋና ጸሎት 8 የእምነታችሁ ዝና በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማ፥ ከሁሉ አስቀድሜ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ስለ ሁላችሁ አምላኬን አመሰግናለሁ። 9 ዘወትር በጸሎቴ እንደማስባችሁ፥ ስለ ልጁ የሚናገረውን ወንጌል በማስተማር በሙሉ ልቤ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። 10 ደግሞ አሁን በመጨረሻ ወደ እናንተ ለመምጣት የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ መንገዴ እንዲቃናልኝ ሁልጊዜ እጸልያለሁ። 11 በእምነት እንድትጸኑ የሚያደርጋችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እመኛለሁ። 12 ይህንንም ማለቴ እኔ በእናንተ እምነት፥ እናንተም በእኔ እምነት እርስ በእርሳችን እንድንጽናና ነው። 13 ወንድሞቼ ሆይ! በሌሎች አሕዛብ መካከል ብዙ አማኞችን እንዳገኘሁ እንዲሁም በእናንተ መካከል አማኞችን ለማግኘት ፈልጌ ነበር፤ ነገር ግን ወደ እናንተ ለመምጣት ብዙ ጊዜ ዐቅጄ እስከ አሁን ያልተሳካልኝ መሆኑን እንድታውቁ እወዳለሁ። 14 የሠለጠኑትንም ሆነ ያልሠለጠኑትን፥ የተማሩትንም ሆነ ያልተማሩትን ሕዝቦች የማስተማር ግዴታ አለብኝ። 15 ስለዚህ ለእናንተም በሮም ለምትኖሩ ወንጌልን ላስተምራችሁ እመኛለሁ። የወንጌል ቃል የእግዚአብሔር ኀይል መሆኑ 16 እኔ በወንጌል ቃል አላፍርም፤ የወንጌል ቃል በመጀመሪያ አይሁድን፥ ቀጥሎም አሕዛብን፥ እንዲሁም የሚያምኑትን ሰዎች ሁሉ ማዳን የሚችል የእግዚአብሔር ኀይል ነው። 17 ጻድቅ በእምነት ሕይወትን ያገኛል ተብሎ ተጽፎአል፤ የእግዚአብሔር ጽድቅም በሥራ ስለ ታየ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ሰው የሚጸድቀው በእምነት ነው። የሰዎች ክፋት 18 ሰዎች በክፋታቸው እውነት እንዳይታወቅ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም ባለመፍራታቸውና በክፋታቸው ምክንያት በሁሉም ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣል። 19 የሚቀጣቸውም ስለ እግዚአብሔር ማወቅ የሚገባቸውን እግዚአብሔር ራሱ ገልጦላቸው ያውቁ ስለ ነበር ነው። 20 ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለሰዎች የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፥ ይኸውም ዘለዓለማዊው ኀይሉና አምላክነቱ እርሱ በፈጠራቸው ነገሮች አማካይነት ግልጥ ሆኖ ስለ ታየ ሰዎች ለሚያጠፉት ጥፋት ምክንያት የላቸውም። 21 እነርሱ እግዚአብሔርን ዐውቀውት ሳለ ለእርሱ እንደ አምላክነቱ የሚገባውን ክብርና ምስጋና አልሰጡትም፤ በሐሳባቸውም ከንቱ ሆኑ፤ የማያስተውል ልቡናቸውም ጨለመ፤ 22 “ጥበበኞች ነን” ሲሉ ሞኞች ሆኑ። 23 የማያልፈውን እግዚአብሔርን በማክበር ፈንታ ኀላፊ በሆነው በሰው ምስል፥ በወፍ፥ አራት እግሮች ባሉአቸው እንስሶች፥ በመሬት ላይ በሚሳቡ እንስሶች መልክ ለተሠራው ምስል ክብርን ሰጡ። 24 ስለዚህ እርስ በርሳቸው በገዛ አካላቸው ላይ አሳፋሪ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ እግዚአብሔር ርኲሰት ለሞላበት ለክፉ ምኞታቸው ተገዢዎች እንዲሆኑ ተዋቸው። 25 ይህም የሆነው የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ስለ ለወጡ፥ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን ስላመለኩና ስለ አገለገሉ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ አሜን። 26 ሰዎች ይህን በማድረጋቸው ምክንያት እግዚአብሔር ለማይገባ አስነዋሪ ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸው እንኳ የተለመደውን ተፈጥሮአዊ ግንኙነት ባልተለመደ ግንኙነት ለወጡት። 27 እንዲሁም ወንዶቹ የተለመደውን ግንኙነት ከሴቶች ጋር ማድረግ ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ስለዚህ ወንዶች ከወንዶች ጋር አሳፋሪ ነገር ፈጸሙ፤ በስሕተታቸውም ምክንያት የሚገባቸውን ቅጣት በሥጋቸው ይቀበላሉ። 28 ሰዎች እግዚአብሔርን ለማወቅ ስላልፈለጉ አስነዋሪ ነገር እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው። 29 ስለዚህ በበደል፥ በክፋት፥ በሥሥት፥ በተንኰል፥ በምቀኝነት፥ በነፍሰገዳይነት፥ በጥል፥ በአታላይነት፥ በክፉ ምኞት ሁሉ የተሞሉ፥ እንዲሁም ሐሜተኞች ናቸው፤ 30 የሰውን ስም የሚያጠፉ፥ እግዚአብሔርን የሚጠሉ፥ ሰውን የሚያዋርዱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክሕተኞች፥ ክፋትን ለማድረግ ዘዴ የሚፈልጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ 31 የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ጨካኞች ናቸው። 32 “እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉ ሁሉ ሞት ይገባቸዋል” የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ ይህን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ማድረግ ብቻም ሳይሆን፥ እንዲህ የሚያደርጉትንም ሰዎች ያበረታታሉ። |