Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ራእይ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


መቶ አርባ አራት ሺህ የእስራኤል ሰዎች

1 ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማእዘኖች ቆመው አየሁ፤ እነርሱ በምድርም ሆነ በባሕር ወይም በዛፍ ላይ ምንም ነፋስ እንዳይነፍስ ከአራቱ አቅጣጫ የሚመጡትን የምድር ነፋሶች ያዙ።

2 የሕያው አምላክን ማኅተም የያዘ ሌላ መልአክም ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤ ምድርንና ባሕርን እንዲጐዱ ሥልጣን ወደ ተሰጣቸው ወደ አራቱ መላእክት ድምፁን ከፍ አድርጎ፥

3 “በአምላካችን አገልጋዮች ግንባር ላይ ማኅተም እስክናትምባቸው ድረስ፥ ምድርንም ሆነ ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጒዱ” ብሎ ጮኸ።

4 የታተሙትንም ሰዎች ቊጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ የታተሙት ሰዎች ቊጥር መቶ አርባ አራት ሺህ ነበር።

5 ከይሁዳ ነገድ የታተሙት ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሮቤል ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥

6 ከአሴር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከምናሴ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥

7 ከስምዖን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥

8 ከዛብሎን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ነበሩ።


ነጭ ልብስ የለበሱ ብዙ ሕዝቦች

9 ከዚህ በኋላ ተመለከትኩ፤ እጅግ ብዙ ሰዎችን አየሁ፤ እነርሱ ከሕዝብና ከነገድ፥ ከወገንና ልዩ ልዩ ቋንቋ ከሚናገሩ ሁሉ የተውጣጡ ነበሩ፤ እነዚህ ነጭ ልብስ ለብሰው፥ የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር፤

10 በታላቅ ድምፅ እየጮኹም፥ “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው!” ይሉ ነበር።

11 መላእክቱ ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶች ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤

12 እንዲህም አሉ፦ “አሜን! ውዳሴ፥ ገናናነት፥ ጥበብ፥ ምስጋና፥ ክብር፥ ኀይል፥ ብርታት ለአምላካችን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን።”

13 ከሽማግሌዎቹ አንዱ ወደ እኔ መለስ ብሎ “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” አለኝ።

14 እኔም “ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ” አልኩት። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል፤

15 ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሆነው ሌሊትና ቀን በመቅደሱ ያገለግሉታል፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም መጠለያቸው ይሆናል።

16 ከእንግዲህ ወዲህ አይርባቸውም፤ አይጠማቸውም፤ ፀሐይ አይመታቸውም፤ ሙቀት አያገኛቸውም፤

17 በዙፋኑ መካከል ያለው በግ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል፤ እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ይጠርግላቸዋል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios