Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ራእይ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


መጽሐፉና በጉ

1 በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ቀኝ እጅ፥ በውስጥና በውጪ የተጻፈበት በሰባት ማኅተም የታሸገ የብራና ጥቅል መጽሐፍ አየሁ፤

2 አንድ ብርቱ መልአክ በታላቅ ድምፅ “ማኅተሞቹን መፍታትና የብራናውን ጥቅል መጽሐፍ መክፈት የሚገባው ማን ነው?” ብሎ ሲናገር አየሁ።

3 ነገር ግን በሰማይም ሆነ በምድር ወይም ከምድር በታች የብራናውን ጥቅል መጽሐፍ መክፈትና ውስጡን መመልከት የተቻለው ማንም አልነበረም።

4 የብራናውን ጥቅል መጽሐፍ መክፈትና ውስጡን መመልከት የሚገባው ስላልተገኘ በጣም አለቀስኩ፤

5 በዚያን ጊዜ ከሽማግሌዎቹ አንዱ “አታልቅስ፤ እነሆ ከይሁዳ ነገድ የሆነው ከዳዊት የትውልድ ሐረግ የተነሣ አንበሳ ድል ነሥቶአል፤ እርሱ የብራናውን ጥቅል መጽሐፍና ሰባቱን ማኅተሞች መክፈት ይችላል” አለኝ።

6 ከዚህ በኋላ በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከል፥ በሽማግሌዎችም መካከል የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ፤ ይህ በግ ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱ ወደ ዓለም ሁሉ የተላኩ ሰባቱ የእግዚአብሔር መንፈሶች ናቸው።

7 በጉ መጣና በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ቀኝ እጅ የብራናውን ጥቅል መጽሐፍ ወሰደ፤

8 የብራናውን ጥቅል መጽሐፍ በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ኻያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት በግንባራቸው ተደፉ፤ እያንዳንዳቸው በገና ይዘው ነበር፤ እንዲሁም የቅዱሳን ጸሎት የሆነው ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ሙዳይ ይዘው ነበር።

9 አዲስ መዝሙርም እንዲህ እያሉ ዘመሩ፦ “በደምህ ከየነገዱ፥ ከየቋንቋው፥ ከየወገኑ፥ ከየሕዝቡ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ለመዋጀት፥ አንተ ስለ ታረድህ የብራናውን ጥቅል መጽሐፍ ለመውሰድና ማኅተሞቹን ለመክፈት የተገባህ ሆነሃል፤

10 ለአምላካችንም የካህናት መንግሥት እንዲሆኑ አድርገሃቸዋል፤ በምድርም ላይ ይነግሣሉ።”

11 ወደዚያም ስመለከት በዙፋኑና በእንስሶቹ በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ብዛታቸውም በብዙ ሺህና በብዙ ሚሊዮን የሚቈጠር ነበር፤

12 በታላቅ ድምፅም፥ “የታረደው በግ ኀይልን፥ ሀብትን፥ ጥበብን፥ ብርታትን፥ ገናናነትን፥ ክብርንና ምስጋናን ለመቀበል የሚገባው ነው” አሉ።

13 በሰማይና በምድር፥ ከምድር በታችና በባሕር፥ በውስጣቸውም ፍጥረቶች ሁሉ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉም ምስጋና፥ ገናናነት፥ ክብርና ኀይል ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን!” ሲሉ ሰማሁ።

14 አራቱ እንስሶችም “አሜን!” አሉ፤ ኻ አራቱ ሽማግሌዎችም በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios