Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ራእይ 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሴቲቱና ዘንዶው

1 ከዚህ በኋላ ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን የለበሰች፥ ጨረቃን ከእግርዋ በታች ያደረገች፥ ዐሥራ ሁለት ኮከቦችን እንደ አክሊል በራስዋ ላይ የደፋች፥ አንዲት ሴት ታየች።

2 እርስዋም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድም ምጥ ይዞአት ተጨንቃ ትጮኽ ነበር፤

3 እንዲሁም ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች የነበሩት ትልቅ ቀይ ዘንዶ ታየ፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ደፍቶ ነበር፤

4 በጅራቱ የኮከቦችን አንድ ሦስተኛ ከሰማይ ስቦ ወደ ምድር ጣላቸው፤ ሴቲቱ በምትወልድበት ጊዜ ልጅዋን ለመዋጥ አስቦ ዘንዶው ልትወልድ ወደተቃረበችው ሴት ከፊት ለፊትዋ ቆመ፤

5 ሴቲቱም ሕዝቦችን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋ ግን ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተወሰደ፤

6 ሴቲቱም ወደ በረሓ ሸሽታ ሄደች፤ እዚያ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን በእንክብካቤ ተይዛ የምትጠበቅበትን ስፍራ እግዚአብሔር አዘጋጅቶላት ነበር።

7 በሰማይ ጦርነት ተነሣ፤ ሚካኤልና የእርሱ መላእክት ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፥ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጉ። ከእርሱ መላእክት ጋር ተዋጉ፤

8 ነገር ግን ዘንዶውና የእርሱ መላእክት ተሸነፉ፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም።

9 ታላቁም ዘንዶ ወደታች ተጣለ፤ እርሱ መላውን ዓለም የሚያስተው ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው እባብ ነው። እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ የእርሱም መላእክት ከእርሱ ጋር አብረው ተጣሉ።

10 ከዚህ በኋላ አንድ ታላቅ ድምፅ ከሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “እነሆ አዳኝነት፥ ኀይል፥ መንግሥትም የአምላካችን ሆኖአል! ሥልጣንም የመሲሑ ሆኖአል! ወንድሞቻችንን በአምላካችን ፊት ቀንና ሌሊት ሲያሳጣቸው የነበረ የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአል፤

11 እነርሱ በበጉ ደምና በተናገሩት የምስክርነት ቃል ድል ነሥተውታል፤ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፤

12 ስለዚህ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሁሉ ደስ ይበላችሁ! ጥቂት ጊዜ ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ ዲያብሎስ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና ምድርና ባሕር ወዮላችሁ!”

13 ዘንዶው ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት፤

14 ሴቲቱ በበረሓ ወደ ተዘጋጀላት ስፍራ በርራ እንድትሄድ የታላቅ ንስር ክንፎች የሚመስሉ ሁለት ክንፎች ተሰጡአት፤ እዚያም ከእባቡ ፊት ርቃ ሦስት ዓመት ተኩል በእንክብካቤ ተይዛ ትጠበቅ ነበር።

15 ሴቲቱ በጐርፍ እንድትወሰድ ብሎ እባቡ የወንዝ ውሃ የሚያኽል ውሃ ከአፉ ተፍቶ በስተኋላዋ አፈሰሰ።

16 ነገር ግን ምድር ሴቲቱን ረዳቻት፤ አፍዋንም ከፈተችና ዘንዶው ከአፉ ተፍቶ ያፈሰሰውን ውሃ መጠጠች።

17 ዘንዶው በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ ከቀሩት የእርስዋ ዘር ጋር ሊዋጋ ሄደ፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና ለኢየሱስ በታማኝነት የሚመሰክሩ ናቸው።

18 ዘንዶውም በባሕሩ ዳር አሸዋ ላይ ቆመ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios