ራእይ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ይህ ራእይ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚሆነውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳያቸው እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስም መልአኩን ልኮ ለአገልጋዩ ለዮሐንስ ይህን ራእይ ገለጠለት። 2 ዮሐንስም ስለ እግዚአብሔር ቃልና ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አስተማረው እውነት፥ እንዲሁም ስላየውም ነገር ሁሉ መሰከረ። 3 ይህ ሁሉ የሚፈጸምበት ጊዜ ቅርብ ስለ ሆነ ይህን የትንቢት ቃል የሚያነብ የተባረከ ነው! እንዲሁም የትንቢቱን ቃል የሚሰሙና በትንቢቱም ውስጥ የተጻፈውን የሚፈጽሙ የተባረኩ ናቸው። ለሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያን የተላከ ሰላምታ 4-5 ከዮሐንስ ለሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያን። ካለው፥ ከነበረውና፥ ከሚመጣው ከእግዚአብሔር፥ በዙፋኑ ፊት ካሉት ከሰባቱ መንፈሶች፥ እንዲሁም ከሞት በመነሣት በኲር ከሆነው የምድር ነገሥታት ገዢ፥ ታማኝ ምስክር ከሆነው፥ ከሚወደንና በደሙ ከኃጢአታችን ነጻ ካወጣን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 6 የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን እንድናገለግል ንጉሦችና ካህናት ላደረገን፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ኀይል ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን። 7 እነሆ በደመና ይመጣል፤ የወጉት ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ሰው ሁሉ ያየዋል፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ምክንያት ያለቅሳሉ፤ ይህ ነገር እውነት ነው፤ አሜን። 8 ያለው፥ የነበረው፥ የሚመጣውም ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር “አልፋና ዖሜጋ፥ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ!” ይላል። የክርስቶስ በራእይ መገለጥ 9 በኢየሱስ ክርስቶስ የመከራውና የመንግሥቱ እንዲሁ የትዕግሥቱ ከእናንተ ጋር ተካፋይ የሆንኩ እኔ ወንድማችሁ ዮሐንስ በእግዚአብሔር ቃልና በኢየሱስ ምስክርነት ምክንያት ታስሬ ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርኩ፤ 10 በጌታ ቀን በመንፈስ ተመስጦ ላይ ሳለሁ የእምቢልታ ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ከበስተኋላዬ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ 11 “የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያን፥ ማለትም ወደ ኤፌሶን፥ ወደ ሰምርኔስ፥ ወደ ጴርጋሞን፥ ወደ ትያጥሮን፥ ወደ ሰርዴስ፥ ወደ ፊላደልፍያና ወደ ሎዶቅያ ላክ።” 12 ማን እንደ ተናገረኝ ለማወቅ ወደ ኋላዬ ዞር አልኩ፤ ዞር ባልኩ ጊዜም ሰባት የወርቅ መቅረዞችን አየሁ፤ 13 በመቅረዞቹ መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፤ እርሱ እስከ እግሩ የሚደርስ ረጅም ልብስ የለበሰ፥ ደረቱን በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበረ። 14 ራሱና የራስ ጠጒሩ በረዶን እንደሚመስል ሱፍ ነጭ ነበር፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ 15 እግሮቹም በእሳት ፍም ውስጥ እንደ ነጠረ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ታላቅ የፏፏቴ ውሃ ድምፅ ነበረ፤ 16 በቀኝ እጁ ሰባት ኮከቦችን ይዞ ነበር፤ በሁለት በኩል ስለት ያለው ሰይፍ ከአፉ ይወጣ ነበር፤ ፊቱም በሙሉ ድምቀቱ እንደሚያበራ ፀሐይ ነበረ። 17 ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ በእግሩ ሥር ወደቅኩ፤ እርሱ ግን ቀኝ እጁን በላዬ ጭኖ እንዲህ አለኝ፤ “አትፍራ፤ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ 18 እኔም ሕያው ነኝ፤ ሞቼ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ፥ ለዘለዓለም ሕያው ነኝ፤ በሞትና በሲኦል ላይ ሥልጣን አለኝ። 19 እንግዲህ ያየኸውን፥ አሁን ያለውንና በኋላ የሚመጣውን ጻፍ። 20 በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ኮከቦችና የሰባቱም የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ኮከቦች የሰባቱ አብያተ ክርስቲያን መላእክት ናቸው፤ ሰባቱ መቅረዞችም ሰባት አብያተ ክርስቲያን ናቸው።” |