መዝሙር 138 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየምስጋና ጸሎት 1 እግዚአብሔር ሆይ! በሙሉ ልቤ አመሰግንሃለሁ፤ በመላእክት ፊት ለአንተ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ። 2 ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህና ስለ እውነተኛነትህ የስምህንና የትእዛዞችህን ከፍተኛነት ስላሳየህ ወደ ተቀደሰው ቤተ መቅደስህ እየሰገድኩ ስምህን አመሰግናለሁ። 3 በጠራሁህ ጊዜ ሰማኸኝ፤ በብርታትህም አበረታኸኝ። 4 እግዚአብሔር ሆይ! የቃልህን ተስፋ ስለ ሰሙ የዓለም ነገሥታት ሁሉ ያመሰግኑሃል። 5 ስላደረግኸው ድንቅ ነገር ሁሉና ስለ ታላቅ ክብርህ ይዘምሩልሃል። 6 ከሁሉ በላይ ከፍ ያልክ ሆነህ ሳለ፥ ትሑታንን ትንከባከባለህ፤ ትዕቢተኞችን ግን ከሩቅ ሆነህ ትመለከታቸዋለህ። 7 መከራ ዙሪያዬን በሚከበኝ ጊዜ መከታ ሆነህ በሕይወት ትጠብቀኛለህ፤ በቊጣ የተነሡብኝ ጠላቶቼን ትቃወማቸዋለህ፤ በኀይልህም ትታደገኛለህ። 8 የገባኸውን ቃል ኪዳን ትፈጽምልኛለህ፤ እግዚአብሔር ሆይ! ፍቅርህ ዘለዓለማዊ ነው፤ የእጅህን ሥራ ወደ ፍጻሜ ሳታደርስ አትተወው። |