Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሚልክያስ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 እግዚአብሔር በነቢዩ በሚልክያስ አማካይነት ለእስራኤል ሕዝብ የተናገረው የትንቢት ቃል ይህ ነው።


እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለው ፍቅር

2 እግዚአብሔር ሕዝቡን “እኔ እናንተን ወድጄአችኋለሁ” ይላል። እናንተ ግን “እንዴት ወደድከን?” ትላላችሁ። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ይመልሳል፥ “ዔሳውና ያዕቆብ ወንድማማቾች ነበሩ፤ እኔ ግን ያዕቆብን ወደድኩ።

3 ዔሳውን ግን ጠላሁ፤ የዔሳውን ኰረብታማ አገር ወደ ምድረ በዳ ለወጥኩ፤ ምድሩንም የቀበሮ መፈንጫ አደረግሁት።”

4 ኤዶማውያን የተባሉ የዔሳው ተወላጆች “ከተሞቻችን ፈራርሰዋል፤ ነገር ግን መልሰን እንሠራቸዋለን” ቢሉ የሠራዊት አምላክ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ ይሠራሉ፤ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ ሕዝቡም ሁሉ አገሪቱን ‘የክፋት ምድር’ ኗሪዎቹንም ‘እግዚአብሔር ለዘለዓለም የተቈጣው ሕዝብ’ ብለው ይጠሯቸዋል።”

5 እናንተም ይህን ሁሉ በዐይናችሁ አይታችሁ “እግዚአብሔር ከእስራኤል ምድር ውጪ እንኳ ኀያል ነው!” ትላላችሁ።


እግዚአብሔር ካህናትን መገሠጹ

6 የሠራዊት አምላክ ካህናቱን እንዲህ ይላቸዋል፦ “ልጅ አባቱን፥ አገልጋይም አሳዳሪ ጌታውን ያከብራል፤ እነሆ፥ እኔ አባታችሁ ከሆንኩ ለምን አታከብሩኝም? ጌታችሁም ከሆንኩ ለምን ክብር አትሰጡኝም? እናንተ የእኔን ስም ንቃችኋል፤ ነገር ግን ‘ስምህን የናቅነው እንዴት ነው?’ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ።

7 የረከሰ ምግብ በመሠዊያዬ ላይ እያኖራችሁ ‘መሠዊያህን ያረከስነው እንዴት ነው?’ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፤ ያረከሳችሁትማ ገበታዬ በዚህ በእናንተ ነገር ይናቃል ብላችሁ ስላሰባችሁ ነው።

8 ለመሆኑ የታወረውን፥ የታመመውንና አንካሳ የሆነውን እንስሳ ለመሥዋዕት ስታቀርቡ በደል የፈጸማችሁ አይመስላችሁምን? ይህን የመሰለ እንስሳ ለአለቃችሁ ገጸ በረከት አድርጋችሁ ብታቀርቡለት፥ ደስ ብሎት የሚቀበላችሁና የሚያመሰግናችሁ ይመስላችኋልን?” ይላል የሠራዊት አምላክ።

9 “ካህናት ሆይ! ይህን ሁሉ ካደረጋችሁ በኋላ የእግዚአብሔርን ቸርነት ብትለምኑ ልመናችሁን የሚቀበል ይመስላችኋልን? በዚህም ስሕተቱ የእናንተ ነው ይላል የሠራዊት አምላክ።”

10 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “በመሠዊያዬ ላይ ከንቱ እሳትን ከምታቃጥሉበት ይልቅ የቤተ መቅደሱን በር የሚዘጋ ምነው ከእናንተ አንድ ሰው እንኳ በተገኘ! በእናንተ ደስ ስለማይለኝ ለእኔ የምታቀርቡትን ቊርባን አልቀበልም፤

11 እነሆ፥ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ዳር እስከ ዳር ለእኔ ክብር ይሰጣሉ፤ በየትኛውም ስፍራ ለእኔ ዕጣን እያጠኑ ንጹሕ መሥዋዕት ያቀርቡልኛል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ያከብሩኛል።

12 እናንተ ግን ‘የእግዚአብሔር መሠዊያ የረከሰ ነው’ ብላችሁ የተናቀ መሥዋዕት ባቀረባችሁ ጊዜ አረከሳችሁት።

13 እነሆ፥ እናንተ እየተሳለቃችሁ ‘ይህ ሁሉ ምን አሰልቺ ነገር ነው!’ ትላላችሁ። የተሰረቀውን፥ አንካሳውን ወይም የታመመውን እንስሳ ለመሥዋዕትነት ታቀርባላችሁ፤ እኔ ይህን የምቀበል ይመስላችኋልን?

14 እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝ፤ ስሜም በሕዝቦች ዘንድ የተከበረስለሆነ፥ ከበግ መንጋዎቹ መካከል አውራ በግ እያለው ለተሳለው ስለት ነውር ያለበትን በግ መሥዋዕት የሚያቀርብልኝ የተረገመ ነው!” ይላል የሠራዊት አምላክ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios