ዘሌዋውያን 27 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለእግዚአብሔር የቀረበውን ስጦታ መዋጀት 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት ተስሎ ሲፈጸምለት፥ ያ የተሳለው ስለት ሰውን ለመስጠት ከሆነ የመዋጀት ዋጋው እንደ ገመትከው ሆኖ እንደሚከተለው ይሁን፦ 3 በቤተ መቅደሱስ በታወቀው ሚዛን ልክ ዕድሜው ከኻያ እስከ ሥልሳ ለሆነ ወንድ 600 ግራም የሚመዝን ጥሬ ብር ይሁን፤ 4 በዚሁ ዕድሜ ክልል ለምትገኝ ሴት ሠላሳ ጥሬ ብር ይሁን፤ 5 ከአምስት እስከ ኻያ ዓመት ለሆነው ወንድ ኻያ ጥሬ ብር ይሁን፤ በዚሁ ዕድሜ ክልል ላለች ሴት ዐሥር ጥሬ ብር ይሁን፤ 6 ዕድሜው ከአንድ ወር እስከ አምስት ዓመት ለሆነ ወንድ አምስት ጥሬ ብር፥ በዚሁ ዕድሜ ክልል ውስጥ ለምትገኝ ሴት ሦስት ጥሬ ብር ይሁን፤ 7 ዕድሜው ከስድሳ ዓመት በላይ ለሆነው ወንድ ዐሥራ አምስት ጥሬ ብር፤ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት በላይ ለሆናት ሴት ዐሥር ጥሬ ብር ይሁን። 8 “ስእለት ያደረገው ሰው ይህን ተመን ለመክፈል የማይችል ሆኖ ከተገኘ ያ ለስጦታ የቀረበውን ሰው ወደ ካህኑ ያምጣው፤ ካህኑም ያ ሰው የሚችለውን ያኽል ገምቶ ዝቅተኛ ዋጋ ያስከፍለው። 9 “ስእለቱ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበው እንስሳ ከሆነ አይዋጅም፤ ለእግዚአብሔር የቀረበው መባ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል። 10 ሰውየውም ለዚያ እንስሳ ሌላ ምትክ ማቅረብ አይገባውም፤ ምትክ አቅርቦ በተገኘ ጊዜ ግን ሁለቱም እንስሶች ለእግዚአብሔር የተለዩ ይሁኑ። 11 ስጦታው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ ለመቅረብ ተቀባይነት የሌለው ንጹሕ ያልሆነ እንስሳ ከሆነ ግን ሰውየው እንስሳውን ወደ ካህኑ ያምጣ፤ 12 ካህኑም የእንስሳውን መልካምነት ወይም መጥፎነት ገምቶ ዋጋውን ይወስን፤ ያም ዋጋ የመጨረሻ ይሆናል፤ 13 ባለቤቱም እንስሳውን መልሶ ለመግዛት ቢፈልግ በዋጋው ላይ በመቶ ኻያ እጅ ይጨምር። 14 “አንድ ሰው ቤቱን ለእግዚአብሔር የተለየ ስጦታ አድርጎ ሲያቀርብ ካህኑ የቤቱን መልካምነትና መጥፎነት ገምቶ ዋጋውን ይወስን፤ ያም ዋጋ የመጨረሻ ይሆናል። 15 ባለንብረቱ ያንን ቤት መልሶ ለመግዛት ቢፈልግ ግን በዋጋው ላይ በመቶ ሃያ እጅ ይጨምር። 16 “አንድ ሰው ከመሬቱ ከፍሎ ለእግዚአብሔር የተለየ ስጦታ አድርጎ ቢያቀርብ፥ ዋጋው መሬቱ በሚቀበለው ዘር መጠን ይወሰን፤ ይኸውም ለእያንዳንዱ ኪሎ ግራም ገብስ ተቀባይ መሬት ኀምሳ ጥሬ ብር ይክፈል። 17 መሬቱን የኢዮቤልዩ ዓመት እንዳለፈ ወዲያውኑ ለይቶ የሰጠ ከሆነ ሙሉውን ዋጋ መክፈል ይኖርበታል። 18 መሬቱን የሰጠው የኢዮቤልዩ ዓመት ካለፈ ዘግይቶ ከሆነ ግን ካህኑ እስከ ተከታዩ የኢዮቤልዩ ዓመት ያለውን ቀሪ ጊዜ በመገመት ዋጋው እንዲቀነስ ያድርግ። 19 መሬቱን የሰጠው ሰው እንደገና መልሶ ለመግዛት ቢፈልግ በዋጋው ላይ በመቶ ኻያ እጅ ጨምሮ ይክፈል። 20 የቀድሞው ባለ ንብረት መሬቱን ከእግዚአብሔር እንደገና ከመዋጀቱ በፊት ለሌላ ሰው ሸጦት ቢገኝ ግን ያንን መሬት እንደገና መልሶ የመዋጀት መብቱን ያጣል፤ 21 ይህ ለቀድሞ ባለቤቱ ለመመለስ የማይችለው መሬትም በተከታዩ በኢዮቤልዩ ዓመት ለእግዚአብሔር የተለየ ቀዋሚ ንብረት እንደ ሆነ ይቀራል፤ እርሱም የካህኑ ድርሻ ይሆናል። 22 “አንድ ሰው ከሌላ ሰው የገዛውን መሬት ለእግዚአብሔር የተለየ ስጦታ አድርጎ ቢያቀርብ፥ 23 ካህኑ ገምግሞ እስከ ተከታዩ የኢዮቤልዩ ዓመት ያለውን ዋጋ ይተምን፤ ሰውየውም በዚያኑ ዕለት ዋጋውን ይክፈል፤ ገንዘቡም ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ ይሆናል። 24 በኢዮቤልዩ ዓመት መሬቱ ቀድሞ ለሸጠው ባለ ንብረት ወይም ለዘሩ ይመለሳል። 25 “ዋጋቸው ሁሉ የሚተመኑት በቤተ መቅደሱ የሰቅል ሚዛን መሠረት ሲሆን አንዱ ሰቅል ሃያ ጌራ (0.6 ግራም) ነው። 26 “በኲር ሆኖ የሚወለድ እንስሳ ቀድሞውኑ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ ማንም ሰው የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጎ ሊያቀርበው አይችልም፤ እንቦሳም ሆነ የበግና የፍየል ግልገሎች አስቀድመው ለእግዚአብሔር የተለዩ ናቸው፤ 27 ንጹሕ ያልሆነ የእንስሳ በኲር ግን በይፋ በታወቀው ዋጋ ላይ በመቶ ኻያ እጅ ተጨምሮበት እንደገና መዋጀት ይችላል፤ ባለቤቱ የማይዋጀው ከሆነ ግን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሌላ ሰው ይሸጥ። 28 “አንድ ሰው የራሱን ሰውም ሆነ እንስሳን ወይም መሬትን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ እንዲሆን ካደረገው በኋላ ፈጽሞ ሊሸጠውም ሆነ መልሶ ሊዋጀው አይገባውም። 29 የሞት ፍርድ የተፈረደበት ሰው እንደገና ሊዋጅ ፈጽሞ አይገባውም፤ እንዲህ ዐይነቱ ሰው መገደል አለበት። 30 “ምድሪቱ የምታስገኘው እህልም ሆነ ፍራፍሬ ከዐሥር አንዱ ለእግዚአብሔር የተለየ ነው። 31 ከእርሱ ማንኛውንም ነገር መልሶ መዋጀት የሚፈልግ ሰው በይፋ በታወቀው ዋጋ ላይ በመቶ ኻያ እጅ ጨምሮ መግዛት ይችላል። 32 ከቤት እንስሶች ከዐሥር አንዱ እጅ የእግዚአብሔር ድርሻ ነው፤ እንስሶች በሚቈጠሩበት ጊዜ ከዐሥር አንዱ ለእግዚአብሔር የተለየ ነው። 33 ባለ ንብረቱ እንስሶቹ በየዐይነቱ በሚመድብበት ጊዜ ነውረኛውን ከደኅነኛው አይለይ፤ በእርሱም ሌላ ምትክ አያድርግ። በአንዱ እንስሳ ሌላ እንስሳ ተክቶ ቢገኝ ግን፥ ሁለቱም እንስሶች ለእግዚአብሔር የተለዩ ይሁኑ፤ እንደገና መዋጀትም የለባቸውም።” 34 ለእስራኤል ሕዝብ ይነግር ዘንድ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ሳለ እግዚአብሔር የሰጠው ትእዛዞች እነዚህ ናቸው። |