ዘሌዋውያን 25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሰባተኛው ዓመት ( ዘዳ. 15፥1-11 ) 1 እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ በሰባተኛው ዓመት ምንም ሳታርሱ ምድሪቱን በማሳረፍ እግዚአብሔርን ታከብራላችሁ። 3 በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዘርህን ትዘራለህ፤ የወይን ተክልህን ትገርዛለህ፤ እህልህን ትሰበስባለህ። 4 ሰባተኛው ዓመት ግን ለእኔ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሆኖ ምድሪቱ ፍጹም ዕረፍት የምታደርግበት ጊዜ ነው። በዚህ ዓመት ዘርህን አትዘራም፤ የወይን ተክልህንም አትገርዝም። 5 ሳይዘራ ገቦ ሆኖ የበቀለውንም እህል አትሰበስብም፤ ካልተገረዘውም የወይን ሐረግ ፍሬውን አትሰበስብም፤ ያ ዓመት ምድሪቱ ፍጹም ዕረፍት የምታደርግበት ጊዜ ነው። 6 በምድር ሰንበት ዓመት የሚበቅለው ሰብል ሁሉ ለአንተ፥ ለወንድ አገልጋይህ፥ ለሴት አገልጋይህ፥ ለቅጥረኛህ፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ጊዜያዊ መጻተኛ ምግብ ይሆናል። 7 ለእንስሶችህና በምድርህ ለሚገኙ አራዊት የሚበቃ ምግብ ታገኛለህ፤ ምድሪቱ የምታስገኘው ነገር ሁሉ ሊበላ ይችላል። የምሕረት ዓመት (ኢዮቤልዩ) 8 “ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመት ቊጠር፥ ጠቅላላ ድምሩም አርባ ዘጠኝ ዓመት ይሆናል፤ 9 ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን በሚውለው የኃጢአት ስርየት ቀን በመላይቱ ምድር የእምቢልታ ድምፅ የሚያሰማ ሰው ትልካለህ፤ 10 በዚህም ሁኔታ ኀምሳኛውን ዓመት ለይታችሁ በምድሪቱ ለሚኖሩት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ ከዚያ በፊት የተሸጠ ማናቸውም መሬት ለባለቤቱ ወይም ለዘሩ ይመለሳል፤ ባርያም ሆኖ ለማገልገል የተሸጠ ሰው ወደ ቤተሰቡ ይመለሳል። 11 በዚህም ዓመት ዘራችሁን አትዘሩም፤ ሳይዘራ ገቦ ሆኖ የበቀለውን እህላችሁን ወይም ካልተገረዘ የወይን ሐረግ ፍሬውን አትሰበስቡም። 12 ዓመቱ በሙሉ ለእናንተ የተቀደሰ ይሆናል፤ እርሻዎቻችሁ ማንም ሳይንከባከባቸው ራሳቸው የሚያስገኙትን ምግብ ብቻ ትበላላችሁ። 13 “ከዚያ በፊት የተሸጠ መሬት ሁሉ በዚሁ ዓመት ለባለቤቱ ይመለስለታል፤ 14 ስለዚህ ወገንህ ለሆነው እስራኤላዊ መሬት ብትሸጥ ወይም ከእርሱ መሬት ብትገዛ የግፍ ሥራ አትሥራ፤ 15 ዋጋውም የሚተመነው ተከታዩ የንብረት መመለሻ ዓመት ከመግባቱ በፊት፥ ምድሪቱ ልታስገኝ በምትችለው ሰብል መጠን ይሆናል። 16 ዓመታቱ ብዙ ቢሆኑ፥ ዋጋው ከፍ ይላል፤ ዓመታቱ ጥቂቶች ከሆኑ ዋጋው ዝቅ ይላል፤ የሚሸጥበት ዋጋ የሚተመነው ምድሪቱ በምታስገኘው ሰብል መጠን ነው፤ 17 አንዱ እስራኤላዊ በሌላው እስራኤላዊ ላይ ግፍ አይሥራ፤ አምላካችሁን ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። በሰባተኛው ዓመት ስለሚያጋጥም ችግር 18 “በምድሪቱ ላይ በሰላም ትኖሩ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት ሁሉ አክብሩ፤ 19 ምድሪቱም ራስዋ በቂ ሰብል ስለምታስገኝ የምትበሉትን ሁሉ አግኝታችሁ በምቾትና በሰላም ትኖራላችሁ። 20 “ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ዘር ካልዘራንና ሰብል ካልሰበሰብን ምን እንበላለን ብላችሁ ብትጠይቁ፤ 21 በስድስተኛው ዓመት እኔ ምድሪቱን እባርካታለሁ፤ ስለዚህም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ሰብል ታስገኛለች፤ 22 በስምንተኛው ዓመት እንኳ ዘራችሁን ስትዘሩ የምትመገቡት ቀድሞ የሰበሰባችሁትን መከር ነው፤ ይህንኑ መከር የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስከምትሰበስቡ ድረስ ትበላላችሁ። የንብረት መመለስ 23 “ምድሪቱ ለዘለቄታ መሸጥ አይገባትም፤ እርስዋ የእኔ እንጂ የእናንተ አይደለችም፤ እናንተ እንደ መጻተኛ ሆናችሁ እንድትጠቀሙባት ብቻ ፈቅጃለሁ። 24 “መሬት በሚሸጥበት ጊዜ የቀድሞ ባለቤቱ መልሶ ለመዋጀት መብት ያለው መሆኑ መታወቅ አለበት። 25 አንድ እስራኤላዊ ድኻ ሆኖ መሬቱን ለመሸጥ ቢገደድ የቅርብ ዘመዱ የሆነ ሰው ሊዋጅለት ይገባዋል። 26 ሊዋጅለት የሚችል የቅርብ ዘመድ ባይኖረው ግን ዘግየት ብሎ ሀብት በሚያገኝበት ጊዜ እርሱ ራሱ መዋጀት ይችላል። 27 ይህንንም ማድረግ በሚችልበት ጊዜ እስከ ተከታዩ የንብረት መመለስ ዓመት ያለውን ዘመን ቈጥሮ ቀሪውን ገንዘብ ለገዛው ሰው ከመለሰለት በኋላ ወደ ርስቱ ይመለስ። 28 ነገር ግን ለመዋጀት የሚያስችል በቂ ገንዘብ ባይኖረው ርስቱ እስከ ተከታዩ የኢዩቤልዩ ዓመት ድረስ በዚያው በገዛው ሰው እጅ ሊቆይለት ይችላል። በዚያም ዓመት ርስቱ ለባለቤቱ ይመለሳል። 29 “አንድ ሰው ቅጽር በተሠራላት ከተማ ውስጥ ቤት ቢሸጥ ከተሸጠበት ዕለት ጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ መልሶ የመዋጀት መብት አለው። 30 ነገር ግን በዓመቱ ውስጥ መልሶ መዋጀት ባይችል፥ መልሶ የመዋጀት መብቱን ያጣል፤ ቤቱም ለገዛው ሰው ወይም ለዘሮቹ ቀዋሚ ንብረት ሆኖ ይቀራል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት እንኳ ለሻጩ አይመለስለትም። 31 ቅጽር ባልተሠራላቸው መንደሮች ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን መሸጥ የሚችሉት ግን የእርሻ መሬቶች በሚሸጡበት ዐይነት ይሆናል፤ ባለ ንብረቱ እንደገና የመዋጀት መብት አለው፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ንብረቱን መመለስ አለበት። 32 ይሁን እንጂ ሌዋውያን ለእነርሱ በተመደቡላቸው ከተሞች የሚገኘውን ንብረት በማንኛውም ጊዜ መልሶ የመዋጀት መብት ይኖራቸዋል። 33 ሌዋውያን በገዛ ከተሞቻቸው የሚሠሩአቸው ቤቶች በእስራኤላውያን መካከል የእነርሱ ቀዋሚ ንብረቶች ናቸው። በእነዚህ ከተሞች ውስጥ አንድ ሌዋዊ ቤት ቢሸጥና መልሶ ለመዋጀት ባይችል በኢዮቤልዩ ዓመት ይመለስለታል፤ 34 ነገር ግን በሌዋውያን ከተሞች ዙሪያ የሚገኝ የግጦሽ ሣር መሬት ፈጽሞ አይሸጥም፤ እርሱ ለዘለዓለም ቀዋሚ ንብረታቸው ነው። ለድኻ ብድር ስለ መስጠት 35 “በአቅራቢያህ የሚኖር እስራኤላዊ ወገንህ ደኽይቶ ራሱን መርዳት የማይችል ቢሆን በአጠገብህ መኖር ይችል ዘንድ ላስጠጋኸው መጻተኛ በምታደርገው ዐይነት የሚያስፈልገውን ሁሉ በፈቃድህ አድርግለት። 36 ወለድ እንዲከፍል አታድርገው፤ እግዚአብሔርን በመፍራት እስራኤላዊ ወገንህ በአጠገብህ እንዲኖር ፍቀድለት። 37 በምታበድረውም ገንዘብ ወለድ አትጠይቀው፤ በምትሸጥለትም ምግብ ትርፍ አትጠይቀው። 38 የከነዓንን ምድር እንድሰጣችሁና አምላካችሁ እንድሆን ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ። የባሪያዎች ነጻ መለቀቅ 39 “በአጠገብህ የሚኖር እስራኤላዊ ወገንህ ድኻ ከመሆኑ የተነሣ እንደ ባሪያ ሆኖ ሊያገለግልህ ራሱን ቢሸጥ፥ ባሪያ የሚሠራውን ሁሉ እንዲሠራ አታድርገው። 40 እስከ ተከታዩ የኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ እንደ ተቀጣሪ አገልጋይ እያገለገለህ እንደ መጻተኛ ይኑር፤ 41 በዚያን ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ተለይቶ ወደ ወገኖቹና ወደ አባቶቹ ንብረት ይመለሳል። 42 እስራኤላውያን የእኔ አገልጋዮች ናቸው፤ እኔ ከግብጽ ምድር ነጻ አውጥቼአቸዋለሁ፤ ስለዚህም ባርያ ሆነው መሸጥ የለባቸውም። 43 እነርሱን በማስጨነቅ አትግዛቸው፤ ነገር ግን እኔን አምላክህን ፍራ። 44 በአካባቢህ ከሚገኙት አሕዛብ መካከል እንዲኖሩህ የምትፈልጋቸውን ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችህ የሚሆኑትን ልትገዛ ትችላለህ። 45 እንዲሁም በመካከላችሁ የሚኖሩትን የመጻተኞችን ልጆች መግዛት ትችላላችሁ፤ በምድራችሁ የተወለዱትም እንደነዚህ ያሉት ልጆች የራሳችሁ ንብረት መሆን ይችላሉ። 46 እነርሱንም በውርስ ለልጆቻችሁ ማስተላለፍ ትችላላችሁ፤ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ አገልጋዮቻችሁ ይሆናሉ፤ ከእስራኤላውያን ወገኖቻችሁ መካከል ግን ማንንም በማስጨነቅ አትግዙ። 47 “ምናልባት በመካከልህ የሚኖር አንድ መጻተኛ ባለጸጋ ሲሆን፥ እስራኤላዊ ወገንህ ደኽይቶ ለዚያ መጻተኛ ወይም ከእርሱ ቤተሰብ ለአንዱ ራሱን በባርነት ያስገዛ ይሆናል። 48 ከተሸጠም በኋላ እንደገና ተዋጅቶ የመመለስ መብት አለው፤ ስለዚህም ከወንድሞቹ አንዱ ሊዋጀው ይችላል፤ 49 አጐቱ፥ የአጐቱ ልጅ ወይም ከቅርብ ዘመዶቹ አንዱ መልሶ ሊዋጀው ይችላል፤ በቂ ገንዘብ ካጠራቀመም የራሱን ነጻነት ራሱ መዋጀት ይችላል። 50 ይህም በሚሆንበት ጊዜ ከገዛው ሰው ጋር ይመካከር፤ ዘመኑንም እርሱ ራሱን ከሸጠበት ዓመት ጀምሮ እስከ ተከታዩ የኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቊጠሩት፤ ስለ እርሱም ነጻ መለቀቅ ተገቢውን ዋጋ በእነዚያ ዓመቶች ውስጥ ተቀጥሮ በሚሠራ ሰው ልክ ይተምኑት። 51 ብዙ ዓመቶች ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቊጥር ከሽያጩ ዋጋ ይመልስ፥ 52 እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂቶች ዓመቶች ቢቀሩ ከእርሱ ጋር ይቈጥራል፤ እንደ ዓመቶቹም መጠን የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። 53 ይህም መሆን ያለበት በዓመት ክፍያ እንደ ተቀጠረ ሰው ታስቦ ነው፤ ጌታው እርሱን በማስጨነቅ መግዛት የለበትም። 54 በዚህ ዐይነት ነጻ ለመውጣት ባይችል፥ በተከታዩ የኢዮቤልዩ ዓመት እርሱና ልጆቹ ነጻ ይለቀቁ። 55 እስራኤላውያን የእኔ አገልጋዮች ስለ ሆኑ እስራኤላዊ የሆነ ማንም ሰው ለዘለቄታው ባርያ ሆኖ መገዛት የለበትም፤ እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ናቸው፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ።” |