Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘሌዋውያን 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ መብራቶች የሚደረግ ጥንቃቄ
( ዘፀ. 27፥20-21 )

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦

2 “በድንኳኑ ውስጥ ያለው መብራት ዘወትር ሲበራ እንዲኖር ለማድረግ ተጨምቆ የተጠለለ ንጹሕ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ እስራኤላውያንን እዘዝ።

3 አሮን በየምሽቱ መብራቱን ያቀጣጥላል፤ እርሱም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ባለው በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ካለው መጋረጃ ውጪ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ንጋት ድረስ ሲበራ ያድራል፤ ይህም ድንጋጌ በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ተጠብቆ ይኖራል።

4 አሮን መብራቶቹን በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ባለሟቋረጥ የሚበሩ መሆናቸውንም ይቈጣጠራል።


ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የተቀደሰ ኅብስት

5 “ዐሥራ ሁለት ኪሎ የላመ ዱቄት ወስደህ ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤

6 ኅብስቱን በእግዚአብሔር ፊት ባለው በንጹሕ ወርቅ በተለበጠው ገበታ ላይ ስድስቱን በአንድ በኩል፥ ስድስቱን በሌላ በኩል በሁለት ረድፍ ደርድረህ አኑር።

7 በእሳት የሚቃጠል ለእግዚአብሔር የቀረበ የተቀደሰ ኅብስት ለመሆኑ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ንጹሕ የሆነ ዕጣን በሁለቱም ረድፍ ላይ አኑር።

8 አሮን ስለ እስራኤል ሕዝብ ሆኖ ኅብስቱን በየሰንበቱ ለሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ያኖረዋል።

9 ይህም የእስራኤል ሕዝብ ዘወትር ሊፈጽሙት የሚገባ የቃል ኪዳን ሥርዓት ነው። ኅብስቱ የአሮንና የልጅ ልጆቹ ድርሻ ይሆናል፤ እነርሱም በተቀደሰ ቦታ ይብሉት፤ እርሱ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል ቅዱስ መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበ በኋላ ለካህናቱ የተለየ ቋሚ ድርሻ ይሆናል።”


በደልና ቅጣት

10 እናቱ እስራኤላዊት፥ አባቱ ግብጻዊ የሆነ አንድ ሰው በእስራኤላውያን መካከል ወጥቶ ከአንድ እስራኤላዊ ጋር ተጣላ፤

11 የእስራኤላዊቱ ልጅ የእግዚአብሔርን ስም ስለ ተሳደበ ወደ ሙሴ አቀረቡት፤ የእናቱም ስም ሰሎሚት የምትባልና ከዳን ነገድ የሆነው የዲብሪ ልጅ ነበረች።

12 የእግዚአብሔር ፈቃድ እስኪገለጥላቸው ድረስ በቊጥጥር ሥር አዋሉት።

13 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤

14 “ያን ሰው ከሰፈር አውጣ፤ ሲሳደብ የሰማው ሰው ሁሉ ያ ሰው በደል የሠራ መሆኑን ለመመስከር እያንዳንዱ እጁን በዚያ ሰው ራስ ላይ ይጫን፤ ከዚያም በኋላ መላው የእስራኤል ሕዝብ በድንጋይ ወግሮ ይግደለው፤

15 እኔን እግዚአብሔርን የሚሰድብ ማንም ሰው ቅጣቱን ይቀበላል፤

16 የእግዚአብሔርን ስም የሚሰድብ ይገደል፤ ማኅበረሰቡ ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት፤ እስራኤላዊም ሆነ መጻተኛ የእግዚአብሔርን ስም ሲሰድብ ይገደል።

17 “ሰውን የሚገድል ማንም ሰው በሞት ይቀጣ፤

18 የሌላን ሰው እንስሳ የገደለ ምትኩን ይክፈል፤ ይህም ዐይነቱ ሥርዓት በሕይወት ምትክ ሕይወት መሆኑ ነው።

19 “ማንም ሰው በሌላ ሰው ላይ ጒዳት ቢያደርስ የዚያኑ ዐይነት ጒዳት ይድረስበት፤

20 የሌላውን ሰው አጥንት ቢሰብር አጥንቱ ይሰበር፤ የሌላውን ሰው ዐይን ቢያወጣ ዐይኑ ይውጣ፤ ጥርስም ቢሰብር ጥርሱ ይሰበር። በሌላ ሰው ላይ ምንም ዐይነት ጒዳት ቢያደርስ የዚያው ዐይነት ጒዳት በእርሱ ላይ ይመለስበት።

21 እንስሳ የሚገድል ምትኩን ይክፈል፤ ሰውን የሚገድል ግን በሞት ይቀጣ።

22 ይህም ሕግ ለሁላችሁም ማለትም ለእናንተ ለእስራኤላውያንም ሆነ፥ በእናንተ መካከል ለሚኖሩት መጻተኞች ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።”

23 ሙሴም ይህን ሁሉ ለሕዝቡ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ ያን ሰው ከሰፈር አወጡና በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ በዚህም ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios