Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘሌዋውያን 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦

2 “ለአሮንና ለልጆቹ እንዲህ በላቸው፦ የተቀደሰ ስሜን እንዳታረክሱ የእስራኤል ልጆች ለይተው ለእኔ የሚያቀርቡትን መባ ሁሉ በአክብሮት ተቀብላችሁ በቅድስና ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

3 ከልጅ ልጆቻችሁ መካከል የረከሰ ሆኖ ሳለ የእስራኤል ልጆች ለእኔ ለይተው ወዳቀረቡት ቅዱስ ስጦታ ደፍሮ ቢቀርብ ከፊቴ ተወግዶ ይጠፋል፤ ይህም ሥርዓት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ተጠብቆ ይኖራል፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

4 “ከአሮን ተወላጆች ማንም ሰው የሥጋ ደዌ በሽታ ወይም ፈሳሽ ነገር ያለበት ከሆነ እስከሚነጻበት ድረስ ከተቀደሰው ነገር አይብላ። በድን በመንካቱ የረከሰውን ነገር የሚነካ ወይም የዘር ፈሳሽ ያለበት

5 እንዲሁም በልቡ የሚሳብ፥ የሚያረክስ ነገርን የሚነካ፥ ወይም ርኲሰቱ ምንም ዐይነት ቢሆን የረከሰውን ሰው የሚነካ፤

6 ማንኛውም ሰው እነዚህን ነገሮች ቢነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ገላውን በውሃ ካልታጠበ በቀር የተቀደሱትን ነገሮች አይብላ።

7 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ግን ንጹሕ ስለሚሆን የእርሱ ድርሻ የሆነውን የተቀደሰ የእህል መባ መብላት ይችላል፤

8 ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የገደለውን የእንስሳ ሥጋ አይብላ፤ እርሱን ቢበላ ያረክሰዋል፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

9 “ካህናት ሁሉ እኔ የሰጠኋቸውን የሥርዓት መመሪያዎች ይጠብቁ፤ ይህን ባያደርጉ ግን ለተቀደሱት የትእዛዝ መመሪያዎች ባለመታዘዛቸው በደል ሆኖባቸው ይሞታሉ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

10 “ከተቀደሰው ስጦታ መብላት የሚችለው የካህን ቤተሰብ የሆነ ሰው ብቻ ነው፤ ሌላ ሰው ግን ከእርሱ አይብላ፤ ከካህኑ ጋር በእንግድነት ወይም ተቀጥሮ የሚኖር አይብላ።

11 ካህኑ በገንዘቡ የገዛው ወይም በቤቱ የተወለደ አገልጋዩ ግን የካህኑ ድርሻ ከሆነው ምግብ ይብላ።

12 ካህን ያልሆነ የውጪ ሰው ያገባች የካህኑ ልጅ ከተቀደሰው ስጦታ አትብላ።

13 ነገር ግን ልጅ ሳትወልድ ባልዋ የሞተባት ወይም ከባልዋ በመፋታት ወደ አባቷ ቤት ተመልሳ መጥታ በጥገኝነት የምትኖር የካህኑ ልጅ በልጅነትዋ ታደርገው እንደ ነበረው ሁሉ የአባቷ ድርሻ ከሆነው ቅዱስ ነገር ትብላ፤ ሆኖም ከካህኑ ቤተሰብ ሌላ ሰው የተቀደሰውን ነገር መብላት የለበትም።

14 “የካህን ቤተሰብ ያልሆነ ማንም ሰው ባለማወቅ ከተቀደሰው ስጦታ በልቶ ቢገኝ የምግቡን ሙሉ ዋጋና አንድ አምስተኛ እጅ ጨምሮ ለካህኑ ይክፈለው።

15 የእስራኤል ሕዝብ ለእግዚአብሔር የሚያመጡአቸውን የተቀደሱ ስጦታዎች፥ ካህናት ማርከስ የለባቸውም፤

16 ይኸውም መብላት ለማይፈቀድለት ሰው ቢሰጡት በደል ሆኖ በዚያ ሰው ላይ ቅጣት ያስከትልበታል፤ ስጦታዎችን ሁሉ የምቀድስ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

17 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

18 “ለአሮንና ለልጆቹ ለመላውም የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ እስራኤላዊ የሆነ ወይም በእስራኤላውያን መካከል የሚኖር መጻተኛ ስእለት ተፈጽሞለት ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጎ የሚቃጠል መሥዋዕት ቢያቀርብ፥

19 መሥዋዕቱም ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ምንም ነውር የሌለበት የከብት፥ የበግ ወይም የፍየል ተባዕት ይሁን።

20 ነውር ያለበትን ማናቸውንም እንስሳ ብታቀርቡ ግን እግዚአብሔር አይቀበለውም።

21 ማንም ሰው ስእለት ተፈጽሞለት ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጎ የአንድነት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ቢያቀርብ፥ ተቀባይነት ማግኘት እንዲችል፥ እንስሳው ምንም ነውር የሌለበት ይሁን።

22 ዕውር፥ ሰባራ ወይም ጉንድሽ የሆነ ወይም የሚመግል ቊስል፥ እከክ ወይም ሽፍታ ያለበት ማናቸውንም እንስሳ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ፤ እንደነዚህ ያሉትን እንስሶች በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ።

23 አካሉ የጐደለ ወይም ቅርጹ የተበላሸ እንስሳ የበጎ ፈቃድ መሥዋዕት ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፤ ነገር ግን ስእለት የተፈጸመለት ሰው መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው አይችልም።

24 ብልቱ የተበላሸ እንስሳ ለእግዚአብሔር በምድርህ መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ።

25 “ከባዕድ ሰው የተገኘውን እንስሳ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ፤ እነዚህን የመሳሰሉ እንስሶች ነውር እንዳለባቸው ስለሚቈጠሩ ተቀባይነት የላቸውም።”

26 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦

27 “እንቦሳ፥ ወይም በግ፥ ወይም ፍየል ሲወለድ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፤ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ ይችላል።

28 “ላምን ከጥጃዋ ጋር፥ በግንም ከግልገልዋ ጋር በአንድ ቀን አትረድ፤

29 ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት በምታቀርብበት ጊዜ ተቀባይነት ታገኝ ዘንድ የመመሪያ ሥርዓቶችን ጠብቅ፤

30 ለተከታዩ ቀን ሳታስተርፍ ሁሉንም በቀረበበት ዕለት ብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

31 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ትእዛዞቼን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤

32 የተቀደሰውን ስሜን አታዋርዱ፤ መላው የእስራኤል ሕዝብ እኔ ቅዱስ መሆኔን ተገንዝበው ያክብሩኝ፤ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤

33 አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios