Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘሌዋውያን 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ለካህናት የተሰጠ መመሪያ

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከሕዝቡ መካከል የሞተውን ሰው አስከሬን በመንካት ስለ ሞተ ሰው ማናቸውም ራሳቸውን እንዳያረክሱ የአሮን ተወላጆች ለሆኑ ካህናት ንገራቸው፤

2 በዝምድና ቅርብ ከሆኑት፥ ከአባቱ፥ ከእናቱ፥ ከወንድ ልጁ፥ ከሴት ልጁ፥ ከወንድሙ፥

3 ወይም ካላገባች እኅቱ በቀር፥

4 በጋብቻ የተዛመዱትን ሰዎች ሬሳ እንኳ በመንካት ራሱን አያርክስ።

5 “ካህናት፥ ለሙታን በማዘን የራስ ጠጒራቸውን አይላጩ፤ ጢማቸውን አሳጥረው አይቊረጡ፤ ፊታቸውንም አይንጩ።

6 የሚቃጠል መሥዋዕትና የምግብ መባ ለእኔ ለአምላካቸው የሚያቀርቡ ካህናት ለእኔ የተለዩና ስሜንም የማያረክሱ መሆን አለባቸው፤ ስለዚህ የተቀደሱ ይሆናሉ።

7 ካህናት ለአምላካቸው ተለይተው የተቀደሱ ስለ ሆኑ፥ አመንዝራ የነበረች ሴት፥ ወይም ክብረ ንጽሕናዋ የተደፈረ ልጃገረድ ወይም አግብታ የፈታች ሴት አያግቡ፤

8 ሕዝቡም ካህኑን ቅዱስ እንደ ሆነ ይቊጠረው፤ እርሱ ለእኔ ለአምላካችሁ የምግብ መባ ያቀርባል፤ እኔ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝ፤

9 የማንኛውም ካህን ሴት ልጅ አመንዝራ ብትሆን አባትዋን ታስነውራለች፤ እርስዋ በእሳት ተቃጥላ ትሙት።

10 “ሊቀ ካህናቱ የቅባት ዘይት በራሱ ላይ የፈሰሰበትና የክህነትንም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ ስለ ሆነ፥ ሰው በሞተ ጊዜ ሐዘኑን ለመግለጥ ጠጒሩን አይላጭ፤ ልብሱንም አይቅደድ፤

11 የማናቸውም ሰው አስከሬን የአባቱም ሆነ ወይም የእናቱ ወደ አለበት ቤት ገብቶ ራሱን አያርክስ፤

12 የእኔ የአምላኩ የክህነት ቅድስና በእርሱ ላይ ስላለ ከመቅደስ ወጥቶ የአምላኩን መቅደስ አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

13 ድንግል የሆነችውን ልጅ ያግባ፤

14 ባልዋ የሞተባትን ወይም አግብታ የተፋታችውን ወይም ክብረ ንጽሕናዋ የተደፈረውን፥ ወይም አመንዝራ የነበረችውን ሴት አያግባ፤ ድንግል የሆነችውን ብቻ ወገኑ ከሆኑ ሕዝብ መካከል መርጦ ያግባ።

15 ይህ ካልሆነ ግን በሕዝቡ መካከል ልጆቹ የረከሱ ይሆናሉ፤ የምቀድሰው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

16 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦

17 “ለአሮን እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘ከዘርህ የአካል ጒድለት ያለበት ማንም ሰው የእኔን የአምላኩን የምግብ መባ ማቅረብ የለበትም፤ ይህም ሥርዓት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ተጠብቆ ይኖራል፤

18 የአካል ጒድለት ያለበት ማንም ሰው፥ ይኸውም ዕውር ወይም አንካሳ የሆነ፥ መልኩ ወይም ቅርጹ የተበላሸ፥

19 እጀ ሰባራ ወይም እግረ ሰባራ የሆነ፥

20 በጀርባው ላይ ጉብር ያለበት ወይም ድንክ፥ የዐይን ሕመም ወይም ልዩ ልዩ ዐይነት የቆዳ በሽታ ያለበት፥ ወይም ጃንደረባ የምግብ ቊርባን ለእኔ ለእግዚአብሔር ሊያቀርብ አይገባውም።

21 በአጠቃላይ ከካህኑ አሮን ዘሮች መካከል የአካል ጒድለት ያለበት ማንም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የምግብ ቊርባን ለአምላኩ ማቅረብ አይችልም።

22 እንዲህ ያለው ሰው ሁለቱንም ዐይነት፥ ማለትም የተቀደሰውንና እጅግ ቅዱስ የሆነውን የምግብ መባ መብላት ይችላል፤

23 ነገር ግን የአካል ጒድለት ስላለበት ወደተቀደሰው መጋረጃ ወይም ወደ መሠዊያው አይቅረብ፤ እነዚህን ለእኔ የተቀደሱትን ነገሮች ማርከስ የለበትም፤ እነርሱንም የቀደስኳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”

24 ሙሴም ይህን ሁሉ ለአሮንና ለአሮን ልጆች፥ ለመላውም የእስራኤል ሕዝብ ተናገረ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios