Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘሌዋውያን 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


አለመታዘዝ የሚያስከትለው ቅጣት

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገር፦ ከእናንተም ሆነ ወይም በመካከላችሁ ከሚኖሩት የውጪ አገር ተወላጆች ውስጥ፥ ማንም ሰው ሞሌክ ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ ከልጆቹ አንዱን አሳልፎ ሰጥቶ ቢገኝ መላው የእስራኤል ሕዝብ በድንጋይ ወግሮ ይግደለው።

3 ማንም ሰው ከልጆቹ አንዱን ለሞሌክ አሳልፎ በመስጠት የተቀደሰውን ድንኳኔን ቢያረክስና ቅዱስ ስሜንም ቢያሰድብ፥ ያ ሰው በእኔ ፊት የተጠላ ይሆናል፤ ከሕዝቡም ለይቼ አጠፋዋለሁ።

4 ነገር ግን ሕዝቡ ያ ሰው ያደረገውን ሁሉ በቸልተኛነት ቢያልፈውና በሞት ባይቀጣው፥

5 እኔ ራሴ በዚያ ሰውና በመላ ቤተሰቡ እንዲሁም ለእኔ ታማኝ ባለመሆን ለሞሌክ በመስገድ ከእርሱ ጋር በሚተባበሩት ሁሉ ላይ መዓቴን አመጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ ከሕዝቡ መካከል ለይቼ አጠፋቸዋለሁ።

6 “ማንም ሰው ምክር ለመጠየቅ ወደ ሙታን መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች ቢሄድ በዚያ ሰው ላይ ቊጣዬን አወርዳለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ፤

7 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሁለንተናችሁን የተቀደሰ አድርጉ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤

8 ኅጎቼን ጠብቁ፤ ፈጽሙአቸውም፤ እኔ እናንተን የምቀድሳችሁ አምላካችሁ ነኝ።”

9 ማንኛውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን ቢሰድብ ይገደል፤ አባቱንና ወይም እናቱን ስለ ሰደበ ሞት የተፈረደበት በራሱ በደል ነው።

10 አንድ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ቢያመነዝር፤ አመንዝራውና አመንዝራይቱ ሁለቱም በሞት ይቀጡ፤

11 አንድ ሰው የአባቱ ሚስት ከሆነችው ሴት ጋር ቢተኛ፥ የአባቱን ኀፍረተ ሥጋ ስለ ገለጠ እርሱና ሴትዮዋ ሁለቱም በሞት ይቀጡ፤ የተፈረደባቸውም በራሳቸው በደል ነው።

12 አንድ ሰው ከምራቱ ጋር ቢያመነዝር ሁለቱም በሞት ይቀጡ፤ የሥጋን ዝምድና በዝሙት በማርከሳቸው ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

13 አንድ ወንድ ከሌላው ወንድ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ቢያደርግ የረከሰ ሥራ ስለ ሠሩ ሁለቱም ይገደሉ፤ ለመሞታቸውም ኀላፊነቱ የራሳቸው ነው።

14 አንድ ሰው እናትና ሴት ልጅዋን ቢያገባ፥ ስለ ፈጸሙት ክፉ ድርጊት ሦስቱም በእሳት ተቃጥለው ይገደሉ፤ እንዲህ ያለው ነገር በመካከላችሁ መፈጸም የለበትም።

15 አንድ ሰው ከእንስሳ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ቢያደርግ፥ እርሱም እንስሳውም ይገደሉ፤

16 አንዲት ሴት ከእንስሳ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ብታደርግ እርስዋም እንስሳውም ይገደሉ፤ ስለ መሞታቸውም ኀላፊነቱ የራሳቸው ይሆናል።

17 አንድ ሰው እኅቱን ወይም በአንድ በኩል ብቻ ከአባቱ ወይም ከእናቱ የተወለደችውን እኅቱን አግብቶ ፍትወታዊ ግንኙነት ቢያደርጉ ይህ አስነዋሪ ነገር በመሆኑ ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ፤ ከእኅቱ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ስላደረገ ፍዳውን ይቀበላል።

18 አንድ ሰው የወር አበባ ካለባት ሴት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ቢያደርግ የወር አበባዋን ኀፍረት ገልጠዋል ሁለቱም ከሕዝቡ ተለይተው ይባረሩ።

19 ከአክስትህ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ፤ በዚህ የሥጋ ዝምድናን ማፍረሳቸው ስለ ሆነ ሁለቱም ፍዳቸውን ይቀበላሉ።

20 አንድ ሰው ከአጐቱ ሚስት ጋር ቢተኛ አጐቱን ያዋረደ ስለ ሆነ እርሱም ሆነ ሴትዮዋ ፍዳቸውን ይቀበላሉ፤ ያለ ልጅም ይቀራሉ።

21 አንድ ሰው የወንድሙን ሚስት ቢያገባ ተግባሩ ርኲሰት ነው፤ የወንድሙንም ክብር ያዋርዳል፤ በዚህም ምክንያት ሁለቱም ልጅ አልባ ሆነው ይቀራሉ።

22 “እኔ እንድትገቡባት የማደርጋት የከነዓን ምድር አንቅራ እንዳትተፋችሁ ሕጌንና ሥርዓቴን ሁሉ ጠብቁ፤

23 በፊታችሁ የማባርራቸውን ሕዝቦች ልማድ አትከተሉ፤ ይህን ሁሉ ነገር ስላደረጉ ተጸየፍኳቸው።

24 ነገር ግን ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ በማርና በወተት የበለጸገችውን ምድር እንድትወርሱ እሰጣችኋለሁ፤ ከሌሎች ሕዝቦች እንድትለዩ ያደረግኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

25 ስለዚህም ንጹሓን በሆኑትና ንጹሓን ባልሆኑት እንስሶችና ወፎች መካከል ልዩነት አድርጉ፤ እኔ ርኩሳን ናቸው ብዬ ለይቼ ባስታወቅኋችሁና በምድር ላይ በሚገኙ እንስሶች፥ ወፎችና ሌሎችም ነገሮች ሁሉ ራሳችሁን አታርክሱ፤

26 እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለ ሆንኩና የእኔ ትሆኑ ዘንድ እናንተን ከአሕዛብ ስለ ለየኋችሁ፥ እናንተ ለእኔ የተቀደሳችሁ ሁኑ።

27 “ወንድ ወይም ሴት የሙታን መናፍስት ጠሪዎች ወይም ጠንቋዮች ቢሆኑ ይገደሉ፤ በድንጋይ ተወግረው ይገደሉ፤ በሞት የሚቀጡትም በራሳቸው በደል ነው።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios