ዘሌዋውያን 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምመሥዋዕት የት ማቅረብ እንደሚገባ 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ 2 “ ‘እግዚአብሔር ያዘዘው ትእዛዝ ይህ ነው’ ብለህ ለአሮንና ለልጆቹ እንዲሁም ለእስራኤላውያን ሁሉ ንገር፤ 3 ከእስራኤል ሕዝብ ማናቸውም ሰው በሬ፥ ወይም በግ፥ ወይም ፍየል ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ በሰፈር ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጪ ቢያርድ፥ 4 በተቀደሰው ስፍራ ለእግዚአብሔር ቊርባን ያቀርብ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ደም በከንቱ እንዳፈሰሰ ተቈጥሮ ይፈረድበታል፤ ከሕዝቡም ይለያል። 5 “ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያመጡታል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር የአንድነት መሥዋዕት አድርጎ ያቀርበዋል። 6 ካህኑ ደሙን በድንኳኑ መግቢያ በመሠዊያው ላይ ይርጭ፤ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ጣፋጭ ሽታ ይሆን ዘንድ ስቡንም ያቃጥለው፤ 7 የእስራኤል ሕዝብ ከእምነታቸው ለሚያርቁአቸው አጋንንት መሥዋዕት አድርገው እንስሶቻቸውን በየሜዳው በማረድ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ አይገባቸውም፤ እስራኤላውያን ይህን ሥርዓት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ይጠብቁት። 8 “ለእነርሱም እንዲህ በላቸው፦ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በማኅበሩ መካከል የሚኖር መጻተኛ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ 9 ለእግዚአብሔር ይሠዋው ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው ያ ሰው ከሕዝቡ ይለይ።’ የደም መብላት መከልከል 10 “ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በሕዝቡ መካከል የሚኖር መጻተኛ ደም ቢበላ በፊቴ የተጠላ ይሆናል፤ ያንንም ሰው ከሕዝቡ እለየዋለሁ። 11 የማንኛውም ሕያው ፍጥረት ሕይወት የሚገኘው በደሙ ውስጥ ነው፤ ደሙ በመሠዊያው ላይ ለእናንተ ኃጢአት ማስተስረያ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ፤ ደምም ሕይወት ስለ ሆነ የኃጢአት ማስተስረያ ነው። 12 ስለዚህ ለእስራኤላውያን የምለው ይህ ነው፤ ከእናንተ ማንም፥ ወይም በመካከላችሁ ከሚኖሩ ማንኛውም መጻተኛ ደም መብላት የለበትም። 13 “ማናቸውም እስራኤላዊ ወይም በሕዝቡ መካከል የሚኖር መጻተኛ የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ አድኖ ቢይዝ ደሙን በመሬት ላይ አፍስሶ በዐፈር ይሸፍነው። 14 የእያንዳንዱ ሕያው ፍጥረት ሕይወት የሚገኘው በደሙ ውስጥ ነው፤ የያንዳንዱ ፍጥረት ሕይወት የሚገኘው በደሙ ስለ ሆነ ደም አትብሉ የእስራኤልን ሕዝብ ብዬ አዝዣለሁ፤ ደምንም የሚበላ ሁሉ ከሕዝቡ ይለያል። 15 “ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም የውጪ አገር ተወላጅ የሆነ ሰው፥ ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የገደለውን የእንስሳ ሥጋ ቢበላ ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱንም ታጥቦ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል፤ 16 ገላውን ባይታጠብና ልብሱን ባያጥብ ግን በኃጢአቱ ቅጣቱን ያገኛል።” |