Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘሌዋውያን 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ርኲሰትን የሚያመጣ የሰውነት ፈሳሽ

1 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

2 “ማንም ሰው ከአባለ ዘሩ የሚወጣ ፈሳሽ ቢኖርበት፥ ያ ፈሳሽ ነገር ርኩስ ነው፤

3 ይህም ማለት ከአባለ ዘሩ ቢፈስ ወይም መፍሰሱን ቢያቆም ያው ርኩስ ነው፤

4 የሚተኛበትም ሆነ የሚቀመጥበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።

5 አልጋውን የሚነካም ሆነ፥

6 ወይም ሰውየው በተቀመጠበት በማንኛውም ነገር ላይ ሁሉ የሚቀመጥ ሰው ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱንም ታጥቦ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሁን።

7 ፈሳሽ ያለበትን ሰው የሚነካ ሁሉ ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱንም ታጥቦ፥ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል።

8 ፈሳሽ ያለበት ሰው ንጹሕ በሆነ ሰው ላይ ምራቁን ቢተፋበት፥ ያ ሰው ልብሱን አጥቦ ሰውነቱንም ታጥቦ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል።

9 ፈሳሽ ያለበት ሰው የሚቀመጥበት ማንኛውም ኮርቻ የረከሰ ነው፤

10 ፈሳሽ ያለበት ሰው የተቀመጠበትን ዕቃ ሁሉ የሚነካ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል፤ ሰውየው የተቀመጠበትን ማንኛውንም ዕቃ የያዘ ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱንም ታጥቦ፥ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል።

11 ፈሳሽ ያለበት ሰው እጁን ሳይታጠብ አንድን ሰው ቢነካ ያ ሰው ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱንም ታጥቦ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

12 ፈሳሽ ያለበት ሰው የነካው ማንኛውም የሸክላ ዕቃ ቢኖር ይሰበር፤ ከእንጨት የተሠራ ዕቃ ሁሉ በውሃ ይታጠብ።

13 “ፈሳሽ ያለበት ሰው ከፈሳሽ በሽታው በዳነ ጊዜ የነጻ እንዲሆን እስከ ሰባት ቀን ድረስ ይቈይ፤ ከዚያም በኋላ ልብሱን ይጠብ፤ በንጹሕ የምንጭ ውሃም ገላውን ይታጠብ፤ የነጻም ይሆናል።

14 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት ዋኖሶች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አምጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ለካህኑ ይስጥ፤

15 ካህኑም ከእነርሱ አንዱን ኃጢአት የሚሰረይበት መሥዋዕት፥ ሌላውንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፤ ስለ ፈሳሹ ነገር ያስተሰርይለታል።

16 “ማንም ሰው ዘሩ ከአባለ ዘሩ ወጥቶ በሚፈስበት ጊዜ መላ ሰውነቱን ታጥቦ እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል።

17 ዘሩ የፈሰሰበት ማንኛውም ልብስም ሆነ ቆዳ በውሃ ይታጠብ እርሱም እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሆናል፤

18 ሴትና ወንድ አብረው ተኝተው በሚነሡበት ጊዜ፥ ሁለቱም ሰውነታቸውን በውሃ ታጥበው እስከ ምሽት ድረስ የረከሱ ይሆናሉ።

19 “ሴት የወር አበባ በምታይበት ጊዜ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ርኩስ ትሆናለች፤ እርስዋንም የሚነካ ማንም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

20 በወር አበባዋ ጊዜ የምትቀመጥበትም ሆነ የምትተኛበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።

21 መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሁን፤

22 የምትቀመጥበትን ነገር የሚነካ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሁን፤

23 የምትተኛበትን ወይም የምትቀመጥበትን ነገር የነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

24 በወር አበባዋ ወቅት ከእርስዋ ጋር የሚተኛ ወንድ ቢኖር እርሱም እንደ እርስዋ የረከሰ ይሆናል፤ ስለዚህም እስከ ሰባት ቀን ድረስ ርኩስ ሆኖ ይቈያል፤ እርሱ የሚተኛበትም አልጋ ርኩስ ይሆናል።

25 “አንዲት ሴት ከወር አበባዋ ወቅት አልፎ ለብዙ ቀን የሚፈስ ወይም ከተመደበው የወር አበባዋ በኋላ ባለማቋረጥ የሚፈስ ደም ቢኖራት፥ ደሙ እስከሚቆምበት ጊዜ ድረስ ልክ በወር አበባዋ ጊዜ እንደ ነበረችበት ሁኔታ የረከሰች ትሆናለች።

26 በዚህም ጊዜ የምትተኛበትም አልጋ ሆነ የምትቀመጥበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።

27 እነርሱንም የሚነካ ሁሉ ስለሚረክስ ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱን ታጥቦ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

28 የደምዋም መፍሰስ ቢቆም እስከ ሰባት ቀን ትቈይ፤ ከዚያም በኋላ የነጻች ትሆናለች።

29 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት ዋኖሶች አምጥታ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለካህኑ ትስጥ፤

30 ካህኑም አንዱን ኃጢአት የሚሰረይበት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ ስለሚፈሰው ርኲሰት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል፥

31 “በመካከላቸው ያለውን ማደሪያዬን በማርከስ እንዳይሞቱ እስራኤላውያንን ከርኲሰት ጠብቃቸው።”

32 ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር ስለሚወጣበትና ስለሚያረክሰው ሰው የተሰጠ ደንብ ይህ ነው።

33 እንዲሁም የወር አበባ በማየት ላይ ስላለች ሴት ወይም ወንድም ሆነ ሴት ፈሳሽ ነገር ከሰውነታቸው በሚወጣ ጊዜ ወይም ካልነጻች ሴት ጋር ስለሚተኛ ወንድ የተሰጠ መመሪያ ይህ ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios