ሰቈቃወ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሩሳሌም መከራና ሐዘን 1 በአንድ ወቅት በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ እንዴት ብቸኛ ሆነች! በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው እንዴት ባል እንደ ሞተባት ሴት ሆነች! በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፥ አሁን እርስዋ እንደ ባሪያ ሆነች። 2 በሌሊት እጅግ ታለቅሳለች፤ እንባዋ በጒንጮችዋ ላይ ይወርዳል፤ ከአፍቃሪዎችዋ ሁሉ እርስዋን የሚያጽናና አንድ እንኳ የለም፤ ወዳጆችዋ የነበሩ ሁሉ ከድተዋታል፤ በጠላትነትም ተነሥተውባታል። 3 የይሁዳ ሕዝብ ከጭንቀትና ከከባድ የባርነት ሥራ በኋላ ወደ ምርኮ ተወሰዱ፤ አሁን እነርሱ በሕዝቦች መካከል ሲኖሩ ዕረፍት አያገኙም፤ እነርሱ በጭንቀት ውስጥ እያሉ አሳዳጆቻቸው ደረሱባቸው። 4 ማንም ሰው በዓላቱን ለማክበር ስለማይመጣ የጽዮን መንገዶች ጭር ይላሉ፤ በሮችዋ ሁሉ ባዶ ናቸው፤ ካህናትዋ ይቃትታሉ ልጃገረዶችዋ በሐዘን ይጨነቃሉ የጽዮንም ዕድል ፈንታ የመረረ ይሆናል። 5 ከኃጢአትዋ ብዛት የተነሣ እግዚአብሔር ችግር እንዲደርስባት አደረገ፤ ጠላቶችዋ ገዢዎችዋ ሆነዋል፤ ልጆችዋም በጠላት ተማርከው ተወስደዋል ጠላቶችዋ ግን ተሳክቶላቸዋል። 6 የኢየሩሳሌም ክብር ሁሉ ጠፍቶአል፤ መሪዎችዋ መሰማሪያ እንዳጡ ዋልያዎች ናቸው፤ አሳዳጆቻቸው ሲያባርሩአቸው ጒልበታቸው እስኪዝል ድረስ ሸሹ። 7 የኢየሩሳሌም ሕዝብ በቀድሞ ጊዜ የነበሩአቸውን የከበሩ ነገሮች በችግራቸውና በጭንቀታቸው ቀን ያስታውሳሉ፤ እነርሱም በጠላት እጅ በወደቁ ጊዜ፥ አንድም ረዳት ባልነበራቸው ጊዜ፥ ጠላቶቻቸው የከተማቸውን ውድቀት ተመልክተው ተሳለቁባቸው። 8 ኢየሩሳሌም ከባድ ኃጢአት ሠርታለች፤ መሳለቂያም ሆናለች፤ ዕርቃንዋን ስላዩአት የሚያከብሩአት ሁሉ ይንቁአታል፤ እርስዋ ራስዋ እየቃተተች ፊትዋን ታዞራለች። 9 አደፍዋ በቀሚስዋ ላይ ይታያል፤ ለወደፊት ምን እንደሚደርስባት አላሰበችም፤ አወዳደቅዋ የሚያሰቅቅ ነው፤ የሚያጽናናት ከቶ የለም፤ ጠላቶችዋ ድል ስላደረግዋት፥ መከራዋን እንዲመለከትላት ወደ እግዚአብሔር ጸለየች። 10 የኢየሩሳሌም ሕዝብ ጠላቶች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የሕዝቡን ሀብት ዘረፉ፤ ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ እንዳይገቡ የተከለከሉ አሕዛብ እንኳ ቤተ መቅደስዋን ሲወሩ ታዩ። 11 ሕዝብዋ ምግብ ማግኘት ፈልገው ይቃትታሉ፤ በሕይወት ለመኖር ሲሉ ሀብታቸውን ሁሉ በምግብ ይለውጣሉ፤ የኢየሩሳሌም ሕዝብ “እግዚአብሔር ሆይ! ተመልከተን! ውርደታችንን ሁሉ እይልን!” እያሉ ይጮኻሉ። 12 እግዚአብሔር ጽኑ ቊጣውን በእኛ ላይ ባወረደበት ቀን በእኛ ላይ እንደ ደረሰው ያለ መከራ የደረሰበት ሰው ያለ እንደ ሆነ እናንተ አላፊ አግዳሚዎች እስቲ እዩ ተመልከቱ! ይህ ሁኔታ ለእናንተ ቀላል ነውን? 13 “ከላይ እሳት ላከ፤ እሳቱም ወደ አጥንታችን ዘለቀ፤ ለእግራችን መረብ ዘረጋ፤ ወደ ኋላም መለሰን፤ ሕሊናችንን አስቶ ቀኑን ሙሉ ሰውነታችን እንዲዝል አደረገ። 14 “በደሎቼ በጫንቃዬ ላይ ታስረዋል፤ እነርሱም በጣም ከባድ ስለ ሆኑ ኀይል አሳጡን፤ ልንቋቋማቸው ለማንችላቸው ጠላቶቻችን አሳልፎ ሰጠን። 15 “እግዚአብሔር ወታደሮቻችንን ከእኛ አስወገደ፤ የጐልማሶቻችንን ኀይል ለማድቀቅ የጦር ሠራዊት ላከብን፤ እግዚአብሔር ባልተደፈረችው ከተማ የሚኖረውን ሕዝባችንን በወይን መጭመቂያ እንደሚረገጥ የወይን ዘለላ ረገጣቸው። 16 “ጠላት ድል ስላደረገ ልጆቻችን ብቸኞች ሆነዋል፤ የሚያበረታታን አጽናኝ ከእኛ ስለ ራቀ፥ እንባ እያፈሰስን እናለቅሳለን። 17 “ጽዮን እጆችዋን ትዘረጋለች፤ ነገር ግን ማንም የሚያጽናናት የለም፤ ጐረቤቶቹ ሁሉ የያዕቆብ ዘር ጠላቶች እንዲሆኑ እግዚአብሔር አዟል። ኢየሩሳሌምም በመካከላቸው እንደ ርኩስ ነገር ሆናለች። 18 “በትእዛዙ ላይ ያመፅሁ ስለ ሆነ፥ እግዚአብሔር ባደረገው ነገር እውነተኛ ነው፤ እናንተ ሕዝቦች ሁሉ አድምጡ ሥቃዬንም ተመልከቱ፤ ወጣቶች ወንዶችና ሴቶች ልጆቼ ተማርከው ተወስደዋል። 19 “ጓደኞቼን ጠራሁ፤ እነርሱ ግን አታለሉኝ። ሕይወታቸውን ለማትረፍ ምግብ በመሻት ላይ ሳሉ ካህናቱና መሪዎቹ ሁሉ በከተማይቱ መንገዶች ሞቱ። 20 “እግዚአብሔር ሆይ! ራሴ እንዴት እንደ ተበጠበጠ ተመልከት! በአንተ ላይ ስላመፅሁ ሆዴ ተሸበረ፤ ልቤም ተሰበረ፤ በመንገድም ሆነ በቤት ውስጥ ሕዝቤ እያለቀ ነው። 21 “ጠላቶቼ ሁሉ ማንም የሚያጽናናኝ ሰው በሌለበት እንዴት እንደምቃትትና እንደምቸገር ሰሙ፤ አንተ ያደረግኸው መሆኑንም ዐውቀው ተደሰቱ፤ በእነርሱ ላይ ልታመጣባቸው የወሰንከውን ቀን አምጣና እንደ እኔ ይሁኑ። 22 “ ክፉ ሥራቸውን ሁሉ ተመልከት፤ በበደሎቼ ሁሉ ምክንያት በእኔ ላይ እንዳደረግኸው በእነርሱም ላይ አድርግ ዘወትር ስለምቃትት ልቤ እየደከመብኝ ነው።” |