Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ኤርምያስ 35 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኤርምያስና ሬካባውያን

1 የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

2 “ወደ ሬካባውያን ቤተሰብ አባሎች ሂድና አነጋግራቸው፤ ከዚያም በኋላ በቤተ መቅደስ ካሉት ክፍሎች ወደ አንዱ አስገብተህ የሚጠጡት የወይን ጠጅ አቅርብላቸው፤”

3 ስለዚህ እኔ የኤርምያስን ልጅ የአዛንያን፥ የሐባዲንያን ልጅ፥ ወንድሞቹንና ልጆቹን ሁሉ የሬካባውያንን ቤተሰብ በሙሉ ወሰድኩ።

4 እነርሱንም ወደ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ሰው የአግዳልያ ልጅ የሐናን ልጆች ወደሚኖሩበት ክፍል አመጣኋቸው፤ ክፍሉም ከባለ ሥልጣኖቹ ክፍል ቀጥሎ ከበር ጠባቂው ከሸሉም ልጅ ከማዕሴያ ክፍል በላይ ነው።

5 በወይን ጠጅ የተሞሉ ማንቈርቈርያና ጽዋዎችን በሬካባውያን ፊት አስቀምጬ “እስቲ የወይን ጠጅ ጠጡ” አልኳቸው።

6 እነርሱ ግን እንዲህ ሲሉ መለሱልኝ፦ “እኛ የወይን ጠጅ አንጠጣም፤ የሬካብ ልጅ የነበረው አባታችን ኢዮናዳብ እኛም ሆንን ዘሮቻችን ሁሉ ምንም ዐይነት የወይን ጠጅ እንዳንጠጣ አዞናል።

7 እንዲሁም መኖሪያ ቤት መሥራት፥ እርሻ ማረስ፥ የወይን ተክል ቦታዎችን ይዘን መንከባከብ እንደማይገባን ነግሮናል፤ እንደ እንግዶች በዚህች ምድር ለብዙ ጊዜ መቀመጥ እንችል ዘንድ በድንኳን መኖር እንደሚገባን አዞናል።

8 ኢዮናዳብ የሰጠንን ትምህርት ሁሉ ተቀብለናል፤ እኛም ሆንን ሚስቶቻችን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም የወይን ጠጅ አንጠጣም፤

9 መኖሪያ ቤት ሳንሠራ በድንኳን እንኖራለን፤ የወይን ተክል ቦታዎችና የእህል እርሻዎችም አይኖሩንም፤

10 በድንኳን ኖረናል፤ የቀድሞ አባታችን ኢዮናዳብ ላዘዘን ቃል ሁሉ በሙሉ ልብ ታዛዦች ሆነናል።

11 ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መጥቶ አገሪቱን በወረረ ጊዜ ከባቢሎናውያንና ከሶርያውያን ሠራዊት ሸሽተን እናመልጥ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣት ወስነናል፤ አሁንም በኢየሩሳሌም የምንኖረው ስለዚህ ነው።”

12-13 ከዚህም በኋላ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም ሕዝብ እንድሄድና እንዲህ ብዬ እንዳዛቸው ነገረኝ፦ “ትምህርትን ተቀብላችሁ ለቃሌ ለመታዘዝ አትችሉምን?

14 የኢዮናዳብ ዘሮች እንኳ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ አባታቸው ያዘዛቸውን ቃል በመጠበቅ እነሆ እስከ አሁን ድረስ ምንም ዐይነት የወይን ጠጅ አይቀምሱም፤ እኔ ግን ሁልጊዜ በመደጋገም እነግራችኋለሁ፤ እናንተ ልትታዘዙኝ አልፈለጋችሁም፤

15 አገልጋዮቼ የሆኑትን ነቢያትን ወደ እናንተ ደጋግሜ ልኬአለሁ፤ እነርሱም ከክፉ ሥራችሁ ተመልሳችሁ ቅን የሆነውን ነገር እንድትሠሩ ነግረዋችኋል፤ ለባዕዳን አማልክት እንዳትሰግዱና የእነርሱም አገልጋዮች እንዳትሆኑ አስጠንቅቀዋችኋል፤ ለእናንተና ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋችሁ ምድር መኖር ትችሉ ዘንድ ይህን ሁሉ አዘዝኳችሁ፤ እናንተ ግን እኔን ለማዳመጥም ሆነ ለምነግራችሁ ቃል ትኲረት ልትሰጡት አልፈለጋችሁም።

16 የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ዘሮች የቀድሞ አባታቸው ያዘዛቸውን ሁሉ ፈጽመዋል፤ እናንተ ሕዝቤ ግን አልታዘዛችሁልኝም።

17 ስለዚህም እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አደርስባችኋለሁ ብዬ የተናገርኩትን ጥፋት ሁሉ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በሆናችሁት ሁሉ ላይ አመጣባችኋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ስነግራችሁ ባለማዳመጣችሁና ስጠራችሁም መልስ ባለመስጠታችሁ ነው።”

18 ከዚህ በኋላ እኔ ኤርምያስ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ለሬካባውያን ወገን የተናገረውን ቃል እንዲህ ብዬ ገለጥኩላቸው፦ “የቀድሞ አባታችሁ ኢዮናዳብ የሰጣችሁን ትእዛዝ ሁሉ ፈጽማችኋል፤ ትምህርቱንም ሁሉ ተከትላችኋል፤ ያዘዛችሁንም ሁሉ አድርጋችኋል፤

19 ስለዚህም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ከዘሩ ምንጊዜም እኔን የሚያገለግል ሰው አይጠፋም።’ ”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios