Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ኢሳይያስ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኢሳይያስ ልጅ ለሕዝቡ የምርኮ ምልክት መሆኑ

1 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ትልቅ ሰሌዳ ወስደህ በጉልህ ጽሑፍ ‘ለማጥፋትና ለምርኮ ፍጠን’ ብለህ ጻፍ።

2 ታማኞች የሆኑ ሁለት ሰዎችን፥ ይኸውም ካህኑን ኦርዮንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርገህ አስቀምጣቸው።”

3 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከነቢይቱ ሚስቴ ጋር ተገናኘሁ፤ እርስዋም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ስሙን ‘ለማጥፋትና ለምርኮ ፍጠን!’ ብለህ ጥራው

4 ልጁም ገና ‘አባባና እማማ’ ብሎ ለመጥራት ከመቻሉ በፊት የደማስቆ ሀብትና የሰማርያ ምርኮ በአሦር ንጉሥ ተመዝብሮ ይወሰዳል።”


የአሶር ንጉሥ አመጣጥ

5 እግዚአብሔር ዳግመኛ ተናገረኝ፤ እንዲህም አለኝ፤

6 “በጸጥታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ምንጭ ውሃ ትተው በንጉሥ ረጺንና በንጉሥ ፋቁሔ ተደስተዋል፤

7 አሁን እኔ የአሦርን ንጉሥ ከኀይለኛ ሠራዊቱ ጋር በእነርሱ ላይ አስነሣዋለሁ፤ የሠራዊቱም አመጣጥ የኤፍራጥስን ወንዝ ሞልቶ እንደሚያጥለቀልቅ ማዕበል ይሆናል።

8 በኀይል እየጐረፈም ወደ ይሁዳ ምድር ይገባል፤ ሁሉን ነገር አጥለቅልቆ ከመሸፈን አልፎ ሙላቱ እስከ አንገት ይደርሳል፤” ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ እርሱም ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ ሰውራ እንደምትጠብቅ ምድሪቱን ይጠብቃል።

9 እናንተ አሕዛብ ጦርነትን ዐወጁ! ነገር ግን ትደመሰሳላችሁ፤ እናንተም የሩቅ አገር ሰዎች ሁሉ አድምጡ፤ ለጦርነትም ተዘጋጁ! ነገር ግን ትደመሰሳላችሁ፤ አሁንም ለጦርነት ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ትደመሰሳላችሁ።

10 የጦር ዕቅድንም አውጡ፤ ነገር ግን እናንተ እንዳሰባችሁት አይሳካላችሁም፤ የፈለጋችሁትን ያኽል ተናገሩ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለ ሆነ ምክራችሁ አይጸናም።


እግዚአብሔር ነቢዩን እንዳስጠነቀቀው

11 ሕዝቡ በሄደበት መንገድ እንዳልሄድ እግዚአብሔር በብርቱ ኀይሉ እንዲህ ብሎ አስጠነቀቀኝ፤

12 “እነርሱ የዐመፅ ሤራ ነው የሚሉትን እናንተም የዐመፅ ሤራ ነው አትበሉ፤ እናንተ እነርሱ የሚፈሩትን ነገር አትፍሩ፤ አትደንግጡም።

13 እኔ የሠራዊት አምላክ ቅዱስ እንደ ሆንኩ አስቡ፤ መፍራት የሚገባችሁም እኔን ብቻ ነው።

14 ከቅድስናዬ ልዕልና የተነሣ ለይሁዳና ለእስራኤል የማሰናከያ ድንጋይና የመውደቂያ አለት እንዲሁም ለኢየሩሳሌም ሕዝብ ወጥመድ እሆንባቸዋለሁ።

15 ስለዚህ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ ወድቀውም ይሰባበራሉ፤ በወጥመድ ተይዘውም ይወሰዳሉ።”


ለጠንቋዮችና ለሙታን ጠሪዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

16 ምስክርነቱን ጠብቀህ ያዝ፤ በደቀ መዛሙርቴ ልብ ውስጥም ሕጉን አትም።

17 ምንም እንኳ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ፊቱን ቢመልስባቸውም እኔ በእርሱ ላይ እተማመናለሁ።

18 እነሆ፥ ልጆቼና እኔ በጽዮን ተራራ ላይ ከሚኖረው ከሠራዊት አምላክ ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጠን የማስጠንቀቂያ ምልክት ነን።

19 “በመንተባተብ የሚቀባጥሩትን ሟርተኞችንና የሙታን መናፍስት ጠሪዎችን ጠይቁ” እያሉ የሚሰብኩአችሁ ወገኖች አሉ፤ ታዲያ፥ ስለ ሕያዋን ሙታንን ከመጠየቅ ይልቅ ሕዝቡ አምላኩን መጠየቅ አይገባውምን?

20 ይህን ቃል ባይናገሩ በእርግጥ የንጋት ብርሃን አይበራላቸውም።


የመከራ ጊዜ

21 ሕዝቡ ተስፋ ቈርጠውና ተርበው በምድሪቱ ላይ ይንከራተታሉ፤ ከመራባቸው የተነሣ ተበሳጭተው ወደ ሰማይ እያንጋጠጡ ንጉሣቸውንና አማልክታቸውን ይራገማሉ።

22 ከዚያ በኋላ ወደ ምድር ሲመለከቱ ሊያዩ የሚችሉት ጭንቀት ጨለማና ጭፍግግ ያለ አስፈሪ ሁኔታን ነው፤ ወደ ድቅድቅ ጨለማም ይጣላሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios