Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ኢሳይያስ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ለንጉሥ አካዝ የመጣለት መልእክት

1 ከዖዝያን ልጅ ከኢዮአታም የተወለደው አካዝ በይሁዳ በነገሠበት ዘመን፥ የሶርያ ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ የረማልያ ልጅ ፋቁሔ ጦርነት ማስነሣት ፈልገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ነገር ግን ኢየሩሳሌምን ድል ሊያደርጉአት አልቻሉም።

2 ሶርያ ከእስራኤል መንግሥት ጋር በመተባበር የጦር ቃል ኪዳን መግባትዋን የይሁዳ ንጉሥ በሰማ ጊዜ እርሱና ሕዝቡ ደንግጠው ልባቸው በነፋስ እንደ ተመታ ዛፍ ተናወጠ።

3 እግዚአብሔርም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፦ “አንተና ልጅህ ሼርያሹብ ንጉሥ አካዝን ለመገናኘት ውጡ፤ እርሱንም ከላይኛው ኩሬ ውሃ በሚመጣበት በልብስ አጣቢዎች ቦታ ታገኙታላችሁ።

4 ረጋ እንዲል፤ እንዳይፈራ፥ በእሳት ተቀጣጥሎ እንደሚነድ እንደ ግንድ ጢስ በሆኑት በሬዚንና በሶርያው በሬማልያ ልጅ ምክንያት እንዳይሸበር ንገረው።

5 በእርግጥ ሶርያውያን ከእስራኤላውያንና ከንጉሣቸው ጋር ግብረ አበር በመሆን ሤራ አድርገዋል፤

6 እነርሱም ይሁዳን ለመውጋት፥ ሕዝቡንም አስጨንቀው የእነርሱ ደጋፊ በማድረግ የጣብኤልን ልጅ ሊያነግሡባቸው ወስነዋል።”

7 ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህ ምክራቸው አይጸናም፤ ከቶ ሊሆን አይችልም፤

8 ስለምን ቢባል፥ የሶርያ ራስ ደማስቆ ስትሆን፥ የደማስቆም ራስ ረጺን ነው፤ ስለ እስራኤልም የሆነ እንደ ሆነ፥ በስልሳ አምስት ዓመቶች ጊዜ ውስጥ ብትንትናቸው ወጥቶ በመንግሥትነት መታወቃቸው ይቀራል።

9 እንዲሁም የእስራኤል ራስ ሰማርያ ስትሆን፥ የሰማርያም ራስ ንጉሥ ፋቁሔ ነው። “ጽኑ እምነት ባይኖራችሁ እናንተም አትጸኑም።”


የዐማኑኤልን መምጣት የሚያሳይ ምልክት

10 እግዚአብሔር እንደገና አካዝን እንዲህ አለው፦

11 “ከምድር ጥልቀትም ሆነ ከሰማይ ከፍታ አንድ ምልክት እንዲሰጥህ አምላክህን እግዚአብሔርን ለምን።”

12 አካዝ ግን “ምልክት ስጠኝ ብዬ አልጠይቅም፤ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ።

13 ለዚህም ኢሳይያስ ሲመልስ እንዲህ አለ “እናንተ የንጉሥ ዳዊት ቤተሰብ ሆይ! ስሙ፤ ሰውን ማሰልቸታችሁ አንሶ እግዚአብሔርንስ ማሳዘን ትፈልጋላችሁን?

14 እንግዲህ እግዚአብሔር ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ‘ዐማኑኤል’ ብላ ትጠራዋለች፤

15 እርሱም ክፉውን ነገር ትቶ መልካሙን ነገር ለመምረጥ የሚያስችል ዕውቀት በሚያገኝበት ጊዜ ማርና ወተት ይመገባል።

16 ታዲያ፥ ይህ ሕፃን በጎውን ከክፉ ለይቶ ከማወቁ በፊት አንተ ትፈራቸው የነበሩ የእነዚህ የሁለት ነገሥታት ምድሮች ፈራርሰው ባድማ ይሆናሉ።

17 “እነሆ እግዚአብሔር እስራኤል ከይሁዳ ከተለየበት ጊዜ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቀውን የመከራ ዘመን በአንተና በሕዝብህ፥ በአባትህም ንጉሣዊ ቤተሰብ ላይ ያመጣል፤ ይኸውም የአሦርን ንጉሥ ያመጣብሃል ማለት ነው።

18 “ያም ዘመን በደረሰ ጊዜ ከዓባይ ወንዝ ዳርቻ ርቀት ግብጻውያን እንደ ዝንብ መንጋ፥ አሦራውያንም ከአገራቸው እንደ ንብ ሠራዊት እየተመሙ ይመጡ ዘንድ እግዚአብሔር ምልክት ይሰጣቸዋል።

19 እነርሱም እየተርመሰመሱ ወጥተው በበረሓው ሸለቆና በአለቱ ዋሻ ውስጥ በእሾኽ ቊጥቋጦና በከብት መሰማሪያ ግጦሽ ላይ ይሰፍራሉ።

20 “ያም ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሠ ነገሥት የራሳችሁን የጢማችሁንና የሰውነታችሁን ሁሉ ጠጒር ይላጫል።

21 “በዚያም ዘመን አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በጎች ይኖሩታል፤

22 እነርሱም ከሚሰጡት ብዙ ወተት የሚያስፈልገውን ምግብ ሁሉ ያገኛል፤ ከዚህም የተነሣ በምድሪቱ ላይ የሚተርፉ ሰዎች ምግባቸው ማርና ወተት ይሆናል።

23 “በዚያም ቀን ግምቱ ሺህ ብር የሚሆን አንድ ሺህ ምርጥ የወይን ተክል እንዲለማ የተደረገበት ቦታ ሁሉ ኲርንችትና እሾኽ ይበቅልበታል።

24 አገሪቱ በኲርንችትና በእሾኽ የተሞላች ስለ ሆነች ሕዝቡ ለአደን የሚወጣው ቀስትና ፍላጻ ይዞ ነው።

25 ቀድሞ በዶማ ተቈፍረው እህል ይበቅልባቸው የነበሩ ኰረብቶች ሁሉ ኲርንችትንና እሾኽን በመፍራት ማንም ወደዚያ አይሄድም፤ ነገር ግን የከብትና የበግ መንጋ መሰማሪያ ብቻ ይሆናሉ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios