Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ኢሳይያስ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር ኢሳይያስን ለነቢይነት እንደ ጠራው

1 ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን አየሁት፤ እርሱም ከፍ ባለና ልዕልና ባለው ዙፋን ላይ ተቀምጦ መጐናጸፊያውም ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።

2 ሱራፌል ተብለው የሚጠሩ መላእክትም በዙሪያው ነበሩ፤ እያንዳንዱ መልአክ ስድስት ክንፍ አለው፤ በሁለቱ ክንፎቹ ፊቱን ይሸፍናል፤ በሁለቱ ክንፎቹ እግሮቹን ሸፍኖ በሁለት ክንፎቹ ይበር ነበር፤

3 አንዱ መልአክ ከሌላው ጋር በመቀባበል፥ “የሠራዊት አምላክ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ነው! ክብሩም በዓለም ሁሉ የተሞላ ነው!” ይሉ ነበር።

4 ከድምፃቸው ጩኸት የተነሣ የቤተ መቅደሱ መድረክ እስከ ሥር መሠረቱ ተናወጠ፤ ቤተ መቅደሱም በጢስ ተሞላ።

5 እኔም “እነሆ አንደበቶቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል የምኖር፥ አንደበቴም የረከሰብኝ ሰው ነኝ፤ ንጉሡን የሠራዊት አምላክን በዐይኖቼ አይቼአለሁና መጥፋቴ ስለ ሆነ ወዮልኝ!” አልኩ።

6 ከነዚያም መላእክት አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፤ ከመሠዊያው የወሰደው የእሳት ፍም የያዘበት ጒጠት በእጁ ነበር።

7 በእሳቱም ፍም ከንፈሮቼን ነክቶ “እነሆ ይህ የእሳት ፍም ከንፈሮችህን ስለ ነካ በደልህ ተወግዶልሃል፤ ኃጢአትህም ይቅር ተብሎልሃል” አለኝ።

8 ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር “ማንን እልካለሁ? መልእክተኛ የሚሆንልንስ ማን ነው?” ሲል ሰማሁት፤ እኔም “እነሆ እኔ እሄዳለሁ! እኔን ላከኝ!” አልኩ።

9 እርሱም “እንግዲያውስ ወደዚህ ሕዝብ ሂድና ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ ነገር ግን ልብ አታደርጉም’ በላቸው” አለኝ።

10 ቀጥሎም “እንዳያዩ፥ እንዳይሰሙና እንዳያስተውሉ በዓይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥ በልባቸው አስተውለው ወደ እኔ ተመልሰው እንዳይፈወሱ ይህን ሕዝብ ልቡ የደነደነ፥ ጆሮው የተደፈነ፥ ዐይኑም የተጨፈነ እንዲሆን አድርግ” አለኝ።

11 እኔም “አቤቱ ጌታ ሆይ፥ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው?” ብዬ ጠየቅሁ። እርሱም “ከተሞች እስኪፈርሱ፥ ቤቶችም የሚኖርባቸው አጥተው ወና እስኪሆኑና አገሪቱም የተፈታች ባድማ እስክትሆን ድረስ ነው።

12 ሕዝቡን ወደ ሩቅ አገር እሰዳለሁ፤ አገሪቱም ባድማ ትሆናለች።

13 ከዐሥሩ አንድ ክፍል ቢተርፍም እንኳ እርሱም እንደ ግራር ወይም እንደ ዋርካ እንደገና ይቃጠላል። ዛፉ ሲቈረጥ ጉቶው ይቀራል። ጉቶውም የተቀደሰ ዘር ነው።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios