Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ኢሳይያስ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ ወይን ቦታ የተነገረ ግጥም

1 ስለ ወይኑ ተክል ለውዴ የፍቅር ዘፈን ልዝፈን ውዴ እጅግ ለም በሆነ ኰረብታ ላይ የወይን ተክል ነበረው።

2 መሬቱን በመቈፈርና ድንጋዩንም ለቅሞ በማውጣት ምርጥ የሆነውን የወይን ሐረግ ተከለበት፤ በመካከሉም መጠበቂያ የሚሆን ማማ ሠራለት፤ ጒድጓድ ቆፍሮም የወይን ፍሬ መጭመቂያ አበጀለት። ከዚያን በኋላ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ ጠበቀ፤ ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ።

3 ስለዚህም ወዳጄ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! በእኔና በወይን ተክል ቦታዬ መካከል ስላለው ነገር እስቲ ፍረዱ፤

4 ለመሆኑ እኔ ለእርሱ ያላደረግኹለት ነገር አለን? ከዚህስ ሌላ ላደርግለት የሚገባ ምን አለ? ታዲያ፥ መልካም ፍሬ ያፈራል ብዬ ስጠብቀው ስለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ?

5 “እንግዲህ በወይን ቦታዬ ላይ የማደርገውን ልንገራችሁ፤ በዙሪያው ያለውን አጥር ነቃቅዬ ቅጽሩን አፈርሳለሁ፤ የምድር አራዊት እንዲበሉትና እንዲፈነጩበት አደርጋለሁ።

6 ከዚያን በኋላ አይገረዝም፤ አይኰተኰትም፤ ስለዚህም አራሙቻ እንዲበቅልበት፥ በኲርንቺትና በእሾኽ እንዲሸፈን አደርጋለሁ፤ ዝናብም እንዳያዘንብበት ደመናን አዛለሁ።”

7 ይህም የሠራዊት አምላክ የወይን ቦታ የተባለው የእስራኤል ሕዝብ ነው፤ እርሱም የይሁዳ ሕዝብ ደስ የሚሰኝበት ተክል ነው። መልካም ሥራ እንዲሠሩ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ በዚህ ፈንታ ነፍሰ ገዳዮች ሆኑ፤ ቅን ፍርድ ይሰጣሉ ብሎ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ እነርሱ ግን ፍርድን በማጓደላቸው የሕዝቡ ጩኸት በዛ።


የሰዎች ክፋት

8 በአገሪቱ ላይ መኖር የሚገባችሁ እናንተ ብቻ መስሎአችሁ፥ ቀድሞ በነበራችሁ ይዞታ ላይ ለመቀላቀል ሰዎችን ሁሉ እያስወጣችሁ ቤትን ከቤት ማያያዝና እርሻንም በእርሻ ላይ ለመቀላቀል ለምትፈልጉ ወዮላችሁ!

9 እነሆ የሠራዊት አምላክ እንዲህ ብሎ በመሐላ ሲያረጋግጥ ሰምቼአለሁ፦ “የተዋቡ ታላላቅ ቤቶች ሁሉ ፈርሰው ወና ይሆናሉ፤ የሚኖርባቸው ሰውም አይገኝም።

10 በሩብ ጋሻ መሬት ላይ የተተከለው የወይን ፍሬ ስምንት ሊትር የወይን ጭማቂ ብቻ ይወጣዋል፤ አንድ መቶ ሰማኒያ ኪሎ እህል የተዘራበትም የእርሻ ምርት ዐሥራ ስምንት ኪሎ ብቻ ይገኝበታል።”

11 ጠጥተው ለመስከር ማልደው ወደ መሸታ ቤት ለሚገሠግሡ፥ የወይን ጠጅ እስኪያቃጥላቸው ሌሊቱንም ሁሉ በዚያው መቈየት ለሚፈልጉ ወዮላቸው!

12 በግብዣቸው ላይ መሰንቆና በገና፥ አታሞና እምቢልታ፥ የወይን ጠጅም ይገኛል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሥራና ውለታውን አላስተዋሉም፤

13 ስለዚህ ሕዝቤ ዕውቀት በማጣታቸው ተማርከው ይወሰዳሉ፤ የተከበሩ መሪዎቻቸው እስከ ሞት ድረስ ይራባሉ፤ ሕዝቡም በውሃ ጥም ይቃጠላል።

14 መቃብር ሆድዋን አስፍታ፥ አፍዋን ከፍታ ትጠብቃቸዋለች፤ የኢየሩሳሌምን መሳፍንትና ተሰብስቦ የሚያወካ ሕዝብዋን ትውጣለች።

15 ሰው ሁሉ የተዋረደ ጐስቋላ ይሆናል፤ ትዕቢተኛ የነበረውም ሁሉ ይዋረዳል።

16 የሠራዊት አምላክ ግን በቅን ፍርዱ ከፍ ከፍ ይላል፤ ቅዱሱም አምላክ በእውነተኛነቱ ቅድስናውን ይገልጣል።

17 የበግ ጠቦቶች፥ ቀድሞ ይሰማሩበት በነበረ ቦታ ይሰማራሉ፤ የሰቡ ፍሪዳዎችና የፍየል ግልገሎች በፈራረሱ ቦታዎች ሣር ይበላሉ።

18 በማታለል ገመድ ኃጢአትን፥ በሠረገላ ገመድ ተንኰልን ለሚጐትቱ ወዮላቸው!

19 “እኛ በዐይናችን እናያት ዘንድ እግዚአብሔር ሊያደርግ ያቀደውን በፍጥነት ያድርግ፤ እናውቃትም ዘንድ የእስራኤል ቅዱስ ያቀዳት ምክር ትፈጸም” ለሚሉ ሁሉ ወዮላቸው!

20 ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑን ጨለማ ለሚያስመስሉ፥ ጣፋጩን መራራ፥ መራራውን ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!

21 ራሳቸውን ብልኆችና ጥበበኞች አድርገው ለሚቈጥሩ ወዮላቸው!

22 የወይን ጠጅ በመጠጣት ጀግኖች፥ የሚያሰክረውንም መጠጥ ለማደባለቅ ደፋሮች ለሆኑ ወዮላቸው!

23 ጉቦ ተቀብለው በደል የሠራውን ሰው ነጻ በመልቀቅ፥ በደል የደረሰበትን ሰው ፍትሕ ለሚነፍጉ ወዮላቸው!

24 የእስራኤል ቅዱስ የሠራዊት አምላክ ያዘዘውን ሕግና ያስተማረውን ሥርዓት ስለ አቃለሉ ገለባና ድርቆሽ በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ የእነርሱም ሥር መሠረት በስብሶ ይጠፋል፤ አበባቸውም ደርቆ እንደ ትቢያ ይበናል።

25 እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ በጣም ተቈጥቶአል፤ በኀያልነቱም ይቀጣቸዋል፤ ተራራዎች ይናወጣሉ፤ የሞቱ ሰዎችም አስከሬን እንደ ጥራጊ በየመንገዱ ዳር ይወድቃል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ የእግዚአብሔር ቊጣ አይበርድም፤ እንደገናም ሊቀጣቸው ተዘጋጅቶአል።

26 እግዚአብሔር አሕዛብን ከሩቅ የሚጠራበት ምልክት ያቆማል፤ ከምድር ዳርቻ ሁሉ በመጨረሻ ይጠራቸዋል፤ እነርሱም ፈጥነው እየተጣደፉ ይመጣሉ።

27 በእነርሱ መካከል ደካማና የሚደናቀፍ አይገኝም፤ የሚያንቀላፋና የሚተኛም የለም፤ ትጥቃቸው አይፈታም፤ የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም።

28 ፍላጻቸው የተሳለ፥ ቀስታቸው የተደገነ ነው፤ የፈረሶቻቸው ኮቴ እንደ ባልጩት ነው፤ የሠረገላዎቻቸውም መንኰራኲር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይገለባበጣል።

29 ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤ እንደ ደቦል አንበሳ ያገሣሉ፤ ዕድናቸውን እያጒረመረሙ በመያዝ ይወስዳሉ፤ ማንም ሊያስጥላቸው አይችልም።

30 በዚያን ቀን እንደ ባሕር ማዕበል እየተመሙ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ይመጡባቸዋል፤ እነሆ ወደ ምድር ቢመለከቱ በጨለማና በመከራ እንደ ተከበቡ ያያሉ፤ ከደመናውም የተነሣ ብርሃኑ ይጨልማል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios