Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ኢሳይያስ 41 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠው ተስፋ

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ በደሴቶች የምትኖሩ ሕዝቦች! ጸጥ ብላችሁ አድምጡ! ሕዝቦች ኀይላቸውን ያድሱ፤ ወደ ፊትም ቀርበው ይናገሩ፤ በፍርድ ሸንጎ በአንድነት እንገናኝ።

2 “ድል አድራጊውን አነሣሥቶ ከምሥራቅ ያመጣ፥ እንዲያገለግለው የጠራው ማነው? ሕዝቦችን አሳልፎ ለእርሱ ይሰጣቸዋል። ነገሥታትንም ያስገዛለታል፤ በሰይፉ እንደ ትቢያ በፍላጻዎቹም እንደ ገለባ ይበታትናቸዋል።

3 ከዚህ በፊት እግሮቹ ሄደውበት በማያውቁት መንገድ እነርሱን በፍጥነት ሲያሳድድ ምንም ጒዳት አይደርስበትም።

4 ይህ እንዲሆን የፈቀደ ማን ነው? የታሪክንስ ሂደት የሚቈጣጠር ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ ነበርኩ፤ በመጨረሻም የምገኝ እኔው ነኝ።

5 “በደሴቶች የሚኖሩ ሕዝቦች እኔ ያደረግኹትን ሁሉ አይተዋል፤ ስለዚህም እጅግ ደንግጠው ተንቀጥቅጠዋል፤ በአንድነትም ተሰብስበው ወደ እኔ መጥተዋል።

6 አንዱ ሌላውን ይረዳል፤ ወንድምም ወንድሙን ‘አይዞህ በርታ፤’ ይለዋል።

7 የእጅ ጥበብ ዐዋቂው ወርቅ አንጥረኛን ያበረታታዋል፤ ጣዖት ጠርቦ በመዶሻ የሚያለሰልሰውም በመስፍ ላይ የሚመታውን ‘አይዞህ በርታ! ብየዳው መልካም ነው!’ ይለዋል። እንዳይንቀሳቀስም ጣዖቱን በምስማር ይቸነክሩታል።”

8 “ነገር ግን አንተ አገልጋዬ እስራኤል ሆይ! ሕዝቤ እንድትሆን የመረጥኩህ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ነህ።

9 ከምድር ዳርቻ አመጣሁህ፥ ከአራቱም ማእዘን ጠራሁህ፤ ‘አገልጋዬ ትሆናለህ’ ብዬ መረጥኩህ እንጂ አልጣልኩህም።

10 እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ! እኔ አምላክህ ነኝ፥ ተስፋ አትቊረጥ! እኔ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፤ ድል ነሺ በሆነ ክንዴ እደግፍሃለሁ።

11 በአንተ ላይ የተቈጡ ሁሉ ተሸንፈው ያፍራሉ፤ አንተንም ለመጒዳት የሚነሡ ጠፍተው እንዳልነበሩ ይሆናሉ።

12 ጠላቶችህን ትፈልጋቸዋለህ፤ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ በአንተ ላይ ጦርነት አስነሥተው የነበሩትም ፈጽሞ እንዳልነበሩ ይሆናሉ።

13 ‘አይዞህ አትፍራ፥ አትደንግጥ፥ ቀኝ እጅህን ይዤ እረዳሃለሁ’ እያልኩ የማበረታታህ፥ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።”

14 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ ትል ደካማ የሆንክ እስራኤል ሆይ! እኔ ስለምረዳህ አትፍራ፤ የምታደግህ የእስራኤል ቅዱስ እኔ ነኝ።

15 እነሆ፥ እኔ እንደ ስለታም፥ አዲስና፥ ጥርስ እንዳለው የመውቂያ መሣሪያ አደርግሃለሁ፤ ተራራዎችንም በማበራየት ታደቃቸዋለህ፤ ኰረብቶችንም ዳምጠህ እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ።

16 ወደ ሰማይ ትበትናቸዋለህ፤ ነፋስም ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በእኔ በእስራኤል ቅዱስም ትመካለህ።

17 “ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ አያገኙም፤ ጒሮሮአቸው ከጥማት የተነሣ ሲደርቅ፥ እኔ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እሰማለሁ፤ እኔም የእስራኤል አምላክ ከቶ አልተዋቸውም።

18 በደረቁ ኰረብቶች ላይ ወንዞች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ በሸለቆዎችም ውስጥ የውሃ ምንጮች ያልፋሉ፤ በረሓዎችንም የኲሬ ውሃ መከማቻ እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ፤ ደረቁም ምድር የምንጭ ውሃ መፍሰሻ ይሆናል።

19 የሊባኖስ ዛፎችን፥ የግራር እንጨቶችን፥ ባርሰነቱንና የወይራ ዛፎችን በበረሓ አበቅላለሁ፤ በምድረ በዳ ዝግባ፥ አስታና ጥድ፥ ወይራ የሞላበት ደን አበቅላለሁ።

20 ይህን የማደርገው የእኔ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገና እኔም የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠርኩት ሁሉም አይተው ያውቁ ዘንድ፥ አስተውለውም ይረዱ ዘንድ ነው።”


እግዚአብሔር ሐሰተኞች አማልክትን መቃወሙ

21 የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፦ እንዲህ ይላል፦ “ጉዳያችሁን አቅርቡ፤ ማስረጃችሁንም አምጡ።

22 ጣዖቶቻችሁንም አምጡና በሚፈጸምበት ጊዜ እንድናውቀው ወደ ፊት የሚሆነውን ሁሉ እስቲ ይንገሩን፤ ወደፊት ውጤታቸው ምን እንደሚሆን አስተውለን እንረዳ ዘንድ የቀድሞዎቹ ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ይንገሩን፤ ወይም ወደፊት ምን እንደሚከሠት ያስረዱን።

23 እናንተም አማልክት መሆናችሁን እንድናውቅ ወደ ፊት የሚሆነውን ሁሉ እስቲ ንገሩን፤ እስቲ መልካም ነገርን አድርጉ፤ ወይም አይተንላችሁ በመፍራት እንድንሸበር ክፉ ነገርን ለማድረስ ሞክሩ።

24 እናንተም ሆናችሁ ድርጊታችሁ በእርግጥ ከንቱ ነው፤ እናንተን ማምለክ የሚሹም አጸያፊዎች ናቸው።

25 “እኔ እግዚአብሔር አንድ መሪ ከሰሜን አስነሥቼአለሁ፤ መጥቶአልም። እርሱም ስሜን የሚጠራና ከፀሐይ መውጫ በኩል የሚመጣ ነው። ሸክላ ሠሪ የሸክላውን ዐፈር እንደሚረግጥ መሪዎችን ይረግጣል።

26 እናውቀው ዘንድና ትክክል ነው እንል ዘንድ ከመጀመሪያ ጀምሮ ይህን የተናገረ ማነው? ስለዚህ ጉዳይ መግለጫ የሰጠ፥ ወይም ያወጀ፥ ከእናንተም አንድ ቃል የተናገረ የለም።

27 በመጀመሪያ ይህን ዜና ለጽዮን የገለጥኩላት እኔ ነኝ፤ ለኢየሩሳሌምም መልካም ዜና አብሣሪ የላክሁላት እኔ ነኝ።

28 ዞር ብዬ በተመለከትኩ ጊዜ ማንም አልነበረም፤ ከአማልክትም መካከል ምክር የሚሰጥ አልነበረም፤ ጥያቄም ስጠይቅ ማንም መልስ የሚሰጥ አልነበረም።

29 ስለዚህ እነዚህ አማልክት ሁሉ ከንቱ ናቸው፤ ምንም ነገር ሊያደርጉ አይችሉም፤ ምስሎቻቸውም እንደ ባዶ ነፋስ ናቸው።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios