ኢሳይያስ 34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ እንደሚፈርድ 1 እናንተ ሕዝቦች ቀርባችሁ አድምጡ! እናንተም ወገኖች ልብ በሉ፤ ምድርና በእርስዋ ያሉ፥ ዓለምና ከእርስዋም የተገኙ ሁሉ ይስሙ። 2 እግዚአብሔር በሕዝቦች ሁሉ ላይ ተቈጥቶአል፤ ኀይለኛ ቊጣውም በሠራዊቶቻቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ ያጠፋዋል፤ በሰይፍም እንዲገደሉ አሳልፎ ይሰጣቸዋል። 3 ሬሳቸው የትም ተጥሎ ይበሰብሳል እንጂ አይቀበርም፤ ተራራዎችም በደማቸው ይጥለቀለቃሉ። 4 ፀሐይ፥ ጨረቃና ከዋክብት ሁሉ ይጠፋሉ፤ ሰማይም እንደ ብራና ተጠቅሎ ይወገዳል፤ ከዋክብትም እንደ ወይንና እንደ በለስ ዛፍ ቅጠል ይረግፋሉ። 5 የእግዚአብሔር ሰይፍ በሰማያት ያቀደውን ካደረገ በኋላ ጥፋትን በወሰነበት በኤዶም ሕዝብ ላይ ለመፍረድ ይወርዳል። 6 ለመሥዋዕት የቀረቡ የበግና የፍየል ጠቦቶች በሚሠዉበት ጊዜ ደማቸውና ስባቸው ሰይፉን እንደሚሸፍን የእርሱም ሰይፍ በኤዶማውያን ደምና ስብ ይሸፈናል፤ እግዚአብሔር ይህን መሥዋዕት በቦጽራ ከተማ፥ ይህንንም ታላቅ ዕርድ በኤዶም ምድር ያቀርባል። 7 የኤዶም ሕዝብ እንደ ጐሽ፥ እንደ ኰርማና እንደ ወይፈን ይወድቃሉ፤ ነገር ግን ከሌሎች ጋር አብረው ይሞታሉ፤ ሀገሪቱም በደማቸው ትነከራለች፤ ምድሪቱም በስባቸው ትዳብራለች። 8 እግዚአብሔር ለጽዮን ለመከላከልና የበቀል እርምጃ ለመውሰድ የሚመጣበትን ዓመትና ቀን ወስኖአል። 9 የኤዶም ጅረቶች ወደ ቅጥራንነት፥ ዐፈሩም ወደ ዲንነት ይለወጣሉ፤ ከዚያም ሀገሪቱ በመላ ትቃጠላለች። 10 ቀንና ሌሊት ትቃጠላለች፤ ጢስም ከእርስዋ መውጣቱን ለዘለዓለም አያቋርጥም፤ ምድሪቱም በዘመናት ሁሉ የማትጠቅም ባድማ ትሆናለች፤ ዳግመኛ በእርስዋ ውስጥ አልፎ የሚሄድ አይኖርም። 11 ጭልፊትና ጃርት ይወርሱአታል፤ የጒጒትና የቊራም መጮኺያ ትሆናለች፤ በላይዋም የመፍረስዋ መለኪያ የሆነ ገመድና የባዶነትዋ መመዘኛ የሆነ ቱምቢ ይዘረጉባታል፤ 12 አገሪቱንም የሚያስተዳድር ንጉሥ አይገኝም፤ መሪዎችም ሁሉ ይወገዳሉ። 13 ቤተ መንግሥቶችዋና በቅጽር የተመሸጉ ከተሞችዋ ሁሉ እሾኽና ሳማ ይበቅልባቸዋል፤ የቀበሮና የሰጐን መኖሪያዎች ይሆናሉ። 14 አነሮች ከጅቦች ጋር አብረው ይኖራሉ፤ አጋንንትም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ የሌሊት ምትሐቶች በፍርስራሾች መካከል ይኖራሉ። 15 በዚያም ጒጒቶች ጎጆ ሠርተው እንቊላል ይጥላሉ፤ እንቁላሎቻቸውንም ፈልፍለው በክንፎቻቸው ጥላ ሥር ይንከባከባሉ፤ አሞራዎችም ከጓደኞቻቸው ጋር በዚያ ይሰባሰባሉ። 16 ስለ ሕያዋን ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር መጽሐፍ የተጻፈውን ፈልጋችሁ አንብቡ፤ ከእነዚህ ፍጥረቶች አንዱ እንኳ አይጠፋም፤ የኑሮ ጓደኛ አጥቶ ብቻውን የሚኖርም አይገኝም፤ እግዚአብሔር ራሱ ይህ እንዲሆን ስላዘዘ እርሱ ራሱ በኅብረት እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል። 17 እግዚአብሔር እያንዳንዳቸው የት መኖር እንደሚገባቸው ወሰነ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ለዘለዓለም ይኖሩበታል። |