ኢሳይያስ 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ስለ ኢትዮጵያውያን የተናገረው ቃል 1 ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የክንፎች ድምፅ ለሚሰማባት አገር ወዮላት! 2 ያቺ አገር መልእክተኞችን ከደንገል በተሠራ ጀልባ በአባይ ወንዝ ላይ ትልካለች፤ ሕዝብዋ ረጃጅሞችና ቆዳቸው ለስላሳ፥ አገራቸው በወንዞች የተከፋፈለች፥ ጠንካሮችና ኀያላን በመሆናቸው በዓለም ሁሉ ወደሚፈሩት ሕዝቦች እናንት ፈጣን መልእክተኞች ሂዱ! 3 በምድር የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ! በተራሮች ጫፍ ላይ የተተከለ የሰንደቅ ዓላማ ምልክት ሲውለበለብ አስተውሉ! መለከት ሲነፋ ስሙ! 4 እግዚአብሔር እንዲህ ብሎኛል፦ “በቀትር ጊዜ በጸጥታ እንደምታበራ ፀሐይ፥ በመከርም ወራት በሞቃት ሌሊት እንደሚታይ ጤዛ ከሰማያዊ መኖሪያዬ ጸጥ ባለ መንፈስ ቊልቊል እመለከታለሁ። 5 የወይን መከር ከመሰብሰቡ በፊት አበቦች ረግፈው የወይን ፍሬ በሚበስልበት ጊዜ የወይን ሐረግ ቅርንጫፎች በስለት ተቈርጠው እንደሚጣሉ እርሱ የዚያችን አገር ሕዝብ ያጠፋል። 6 የወታደሮቻቸው ሬሳ ለወፎችና ለምድረ በዳ አራዊት ምግብ ይሆናል፤ በበጋ ወፎች፥ በክረምትም አራዊት ይቀራመቱታል።” 7 የሠራዊት አምላክ በዓለም ሁሉ የመፈራት ግርማ ካላቸው፥ ቆዳቸው ለስላሳ፥ ቁመታቸው ረጅም ኀያላንና ብርቱዎች ከሆኑት፥ በወንዞች የተከፋፈለች ምድር ካላቸው ከእነዚያ ሕዝብ መባ የሚቀበልበት ጊዜ ይመጣል፤ እነርሱም የሠራዊት አምላክ ወደሚመለክባት ወደ ጽዮን ኰረብታ ይመጣሉ። |