ኢሳይያስ 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሞአብ ተስፋቢስነት 1 የሞአብ ሕዝብ ሆይ! በጽዮን ተራራ ላይ ለሚገኘው ለሀገሪቱ መሪ ከሴላ በበረሓው በኩል ጠቦቶችን እጅ መንሻ አድርጋችሁ ላኩለት። 2 የአርኖንን ወንዝ የሚሻገሩ የሞአብ ሴቶች ከጎጆዎቻቸው ተበታትነው ክንፎቻቸውን እያራገቡ ወዲያና ወዲህ እንደሚንከራተቱ የወፍ መንጋዎች ናቸው። 3 የሞአብ መልእክተኞች ለይሁዳ ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ “ምን ማድረግ እንደሚገባን ምከሩን፤ በቀትር ጊዜ የእናንተ ጥላ እንደ ሌሊት ጨለማ ይከልለን። 4 የሞአብ ስደተኞች በመካከላችሁ ይኑሩ፤ ሊያጠፉአቸው ከሚፈልጉ ወገኖች መጠጊያ ሁኑአቸው።” ጨቋኞች ከእንግዲህ ወዲያ አይኖሩም፤ ያገር መፈራረስም ያከትማል። ወራሪዎችም ይወገዳሉ። 5 በዚያን ጊዜ አንድ መንግሥት በዘለዓለማዊ ፍቅር ይመሠረታል፤ በዙፋኑም ላይ ከዳዊት ዘር አንድ ታማኝ የሆነ፥ ፍትሕን የሚፈልግና ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ፈጣን የሆነ ንጉሥ ይቀመጥበታል። 6 የይሁዳ ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ “የሞአብ ሕዝብ ምን ያኽል ኩራተኛ መሆኑን፥ ትዕቢተኛነቱን፥ ዕብሪተኛነቱንና ንቀቱን ሰምተናል፤ ነገር ግን ፉከራው ሁሉ ከንቱ ነው።” 7 ስለዚህ ሞአብ ታልቅስ፤ ሰዎችም ሁሉ ስለ ሞአብ ያልቅሱ፤ በቂርሔሬስ ከተማ የነበረው ምርጥ ምግብ ትዝ እያላቸው በታላቅ ሐዘን ያለቅሳሉ። 8 የሀሴቦን እርሻዎችና የሲብማ የወይን ተክል ቦታዎች ተደምስሰዋል፤ እነዚህ የወይን ተክል ቦታዎች የአሕዛብ መሪዎችን የሚያሰክር የወይን ጠጅ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ነበሩ፤ ከዚያ በፊት የእነዚያ የወይን ተክሎች ሐረግ እስከ ያዕዜር ከተማ ድረስ የተንሰራፋ ነበር፤ እንዲሁም በስተ ምዕራብ እስከ ሙት ባሕር ማዶና በስተ ምሥራቅም እስከ በረሓው ይደርስ ነበር። 9 ስለ ያዕዜር እንደማለቅስ ስለ ሲብማ የወይን ሐረጎችም አለቅሳለሁ፤ ስለ ሐሴቦንና ስለ ኤልዓሌ እንባዬ ይረግፋል፤ ሕዝቡ የሚደሰትበት መከር አልተገኘባቸውም፤ 10 እነሆ በፍሬያማው የእርሻ ቦታ አንድ እንኳ ደስተኛ የለም፤ በወይን ተክል ቦታዎች የእልልታና የዝማሬ ድምፅ አይሰማም፤ የወይን ጠጅ ለመጥመቅ የወይን ፍሬ የሚጨምቅ የለም፤ እግዚአብሔር የደስታ እልልታን ሁሉ እንዲቆም አድርጎአል። 11 ስለዚህ ልቤ ለሞአብ፥ ነፍሴም ለቂርሔሬስ ይታወካሉ። 12 የሞአብ ሕዝቦች የጣዖት ቤተ መቅደሶቻቸውና መስገጃዎቻቸው ወደተሠሩበት ተራራ ለጸሎት በመመላለስ ሰውነታቸውን አድክመዋል፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ ምንም ውጤት አያስገኝላቸውም። 13 እግዚአብሔር ስለ ሞአብ በቅድሚያ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ 14 አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የአንድ ጊዜያዊ የቅጥር ሠራተኛ የሥራ ጊዜ እንደሚቋረጥ የሞአብ ክብርና ብዙ ሕዝቦችዋ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይዋረዳል፤ ከሕዝቧ የተረፉትም በጣም ጥቂቶችና ደካሞች ይሆናሉ።” |