ኢሳይያስ 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየምስጋና መዝሙር 1 በዚያን ዘመን እንዲህ ብለህ ትዘምራለህ፦ “ጌታ ሆይ! ቀድሞ ተቈጥተኸኝ ነበር፤ አሁን ግን ቊጣህን መልሰህ ስላጽናናኸኝ አመሰግንሃለሁ። 2 በእርግጥ እግዚአብሔር መድኃኒቴ ነው፤ በእርሱ ስለምተማመን የሚያስፈራኝ የለም፤ እግዚአብሔር አምላክ ኀይሌና ብርታቴ ነው፤ እርሱም መድኃኒቴ ሆኖአል። 3 ከደኅንነት ምንጭ ውሃ በደስታ ትቀዳላችሁ።” 4 በዚያን ቀን እንዲህ ትላላችሁ፦ “እግዚአብሔርን አመስግኑ! ስሙንም አክብሩ! በሕዝቦች መካከል እርሱ ያደረገውን ተናገሩ! ስለ ገናናነቱም መስክሩ! 5 ስለ ታላቅ ሥራውም ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ይህም ታላቅ ሥራው በዓለም ሁሉ እንዲታወቅ አድርጉ። 6 በእናንተ መካከል ያለው የእስራኤል ቅዱስ ታላቅ ስለ ሆነ በጽዮን የምትኖሩ ሁሉ ‘እልል’ በሉ!” |