Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ኢሳይያስ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሰላም የሰፈነበት መንግሥት

1 ግንድ እንደሚያቈጠቊጥና ከስሩም ቅርንጫፍ እንደሚያበቅል እንዲሁም ከእሴይ (ከዳዊት ንጉሣዊ) ዘር አንድ ንጉሥ ይወጣል።

2 የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ይኖራል፤ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኀይል መንፈስ፥ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።

3 እግዚአብሔርን በመፍራት ደስ ይለዋል፤ በሚያየው ብቻ አይፈርድም፤ ወይም በሚሰማው ብቻ አይበይንም።

4 ነገር ግን በእውነት ለድኾች ይፈርዳል፤ ረዳት ለሌላቸውም ወገኖች ተከላካይ በመሆን መብታቸውን ያስከብራል፤ በበትር እንደሚመታ፥ መረን በተለቀቁት ላይ ይፈርዳል፤ በቃሉም ክፉዎችን ያጠፋል።

5 ሕዝቡን የሚያስተዳድርበት የወገቡ መታጠቂያ እውነት፥ የጐኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል።

6 ተኲላና በግ በአንድነት ይኖራሉ፤ ነብርም ከፍየል ግልገሎች ጋር አብሮ ይመሰጋል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል አብረው ይመገባሉ፤ ትንሽ ልጅም እየመራ ይጠብቃቸዋል።

7 ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፤ ጥጆቻቸውና ግልገሎቻቸውም አብረው ይመሰጋሉ፤ አንበሶችም እንደ በሬ ገለባ ይበላሉ።

8 ጡት የሚጠባው ሕፃን በእባብ ጒድጓድ አጠገብ ይጫወታል፤ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኚት ቤት ላይ እጁን ያኖራል።

9 በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ምንም ጒዳት አይደርስም፤ ባሕር በውሃ እንደሚሞላ ምድርም እግዚአብሔርን በሚያውቁና በሚያከብሩ ሰዎች ትሞላለች።


በሕይወት የተረፉት ስደተኞች መመለስ

10 በዚያን ጊዜ የእሴይ (የዳዊት) ዘር ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል፤ ሕዝቦች እርሱን ይፈልጉታል፤ መኖሪያውም የተከበረ ይሆናል።

11 በዚያን ጊዜ ጌታ እንደገና የኀይል ሥራ ይሠራል፤ ይኸውም በአሦር፥ በግብጽ፥ በጳጥሮስ አገሮች፥ በኢትዮጵያ፥ በዔላም፥ በባቢሎንና በሐማት እንዲሁም በባሕር ጠረፍ አገሮችና በደሴቶች ሁሉ የሚኖሩትን የቀሩት ወገኖቹን ወደ አገራቸው ይመልሳቸዋል።

12 በዚያን ጊዜ ጌታ በመላው ዓለም ተበታትነው ይኖሩ የነበሩትን የእስራኤልንና የይሁዳን ሕዝብ ከአራቱ ማእዘን ሰብስቦ ያመጣቸው መሆኑን ለመንግሥታት ሁሉ የሚያሳውቅበትን አርማ ከፍ አድርጎ ያቆማል።

13 ከዚያን በኋላ የእስራኤል መንግሥት በይሁዳ ላይ ያለውን ምቀኝነት ይተዋል፤ ይሁዳም በእስራኤል ላይ ያለውን ጠላትነትና ጥላቻ ያቆማል።

14 ሁለቱም ተባብረው በምዕራብ በኩል በፍልስጥኤማውያን ላይ ይነሣሉ፤ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩ ሕዝቦችንም ሀብት ይዘርፋሉ፤ የኤዶምንና የሞአብን ሕዝብ ድል ይነሣሉ፤ የዐሞንም ሕዝብ ለእነርሱ ታዛዦች ይሆናሉ።

15 እግዚአብሔር የግብጽን ባሕረ ልሳን ያደርቃል፤ ማንም ሰው በእግሩ መሻገር እንዲችል የኤፍራጥስን ወንዝ በኀይለኛ ነፋስ መትቶ ወደ ትናንሽ ሰባት ጅረቶች ይከፋፍለዋል።

16 እግዚአብሔር የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብጽ በወጡ ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ከጥፋት የተረፉት የእስራኤል ሕዝብ ከአሦር የሚወጡበትን መንገድ ያዘጋጅላቸዋል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios