ኢሳይያስ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ዖዝያን፥ ኢዮአታም፥ አካዝና ሕዝቅያስ የይሁዳ ነገሥታት ሆነው በነገሡባቸው ዘመናት የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ ይህ ነው፦ እግዚአብሔር ሕዝቡን መገሠጹ 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰማያት ሆይ! ስሙ፤ ምድርም አድምጪ፤ ተንከባክቤ ያሳደግኋቸው ልጆች ዐመፀኞች ሆኑብኝ፤ 3 በሬ ባለቤቱን ያውቃል፤ አህያም የጌታውን ጋጥ ያውቃል፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ምንም አያውቅም፤ ሕዝቤም አያስተውልም።” 4 እናንተ ኃጢአተኞች በደልን የተሸከማችሁ ወገኖች! የክፉ አድራጊዎችም ትውልድ! ሕይወታችሁ የተበላሸ፥ እግዚአብሔርን የተዋችሁና የእስራኤልን ቅዱስ የናቃችሁ በእርሱም ላይ ጀርባችሁን ያዞራችሁ ናችሁ። 5 በዐመፅ ላይ ዐመፅ ጨምራችሁ እንደገና መቀጣት የምትፈልጉት ለምንድን ነው? ራሳችሁ ለሕመም፥ ልባችሁም ሁሉ ለድካም የተጋለጠ ሆኖአል። 6 ከዚህም የተነሣ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጠጒር ድረስ ጤናማ የሆነ የአካል ክፍል የላችሁም፤ ቊስልና እባጭ መግልም የሞላበት ሆኖአል፤ ይህም ቊስላችሁ አልፈረጠም፤ አልታሰረም፤ ወይም በዘይት አለሰለሰም። 7 እነሆ አገራችሁ ምድረ በዳ ሆናለች፤ ከተሞቻችሁም በእሳት ጋይተዋል፤ የእርሻችሁም ቦታ ዐይናችሁ እያየ የውጪ ጠላት ይወስደዋል፤ ሁሉንም ነገር አጥፍቶ ምድራችሁን ውድማ ያደርጋታል። 8 የጽዮን ልጅ በወይን አትክልት ቦታ ውስጥ እንዳለ ዳስ በዱባ ተክል ውስጥ እንዳለ ጎጆና እንደ ተከበበች ከተማ ሆናለች 9 የሠራዊት አምላክ ከጥፋት የሚተርፍ ዘር ባያስቀርልንማ ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን፥ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር። 10 እናንተ የሰዶም ገዢዎች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ! የአምላካችንን ትምህርት አድምጡ፤ 11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይረባኛል? እስከ አሁን ያቀረባችሁልኝ የአውራ በግ፥ የተቃጠለ መሥዋዕትና የፍሪዳ ስብ በቅቶኛል፤ በኰርማና በበግ ጠቦት፥ በአውራ ፍየልም ደም አልደሰትም። 12 እኔን ለመገናኘት እንድትመጡና የመቅደሴን አደባባይ እንድትረግጡ ማን ጠየቃችሁ? 13 ይህን ዐይነት ከንቱ መባ ከእንግዲህ ወዲህ አታቅርቡ፤ የምታጥኑት ዕጣን በፊቴ አጸያፊ ነው፤ አዲስ ጨረቃ የምትወጣበት የወር መባቻችሁና ሰንበቶቻችሁ፥ መንፈሳዊ ስብሰባዎቻችሁም በኃጢአት የተበከሉ ስለ ሆኑ አልወደድሁላችሁም። 14 አዲስ ጨረቃ የምትወጣበትን የወር መባቻችሁንና በዓሎቻችሁን ጠልቻለሁ፤ እነርሱ እንደ ከባድ ሸክም ስለ ሆኑብኝ ልታገሣቸው አልችልም። 15 “እጆቻችሁን ወደ እኔ ለጸሎት ብትዘረጉ፥ ወደ እናንተ አልመለከትም፤ እጆቻችሁ በደም የተበከሉ ስለ ሆኑ የቱንም ያኽል ልመና ብታበዙ አልሰማችሁም፤ 16 ይልቁንስ ታጥባችሁ ንጹሕ ሁኑ፤ ክፉ ሥራችሁን ሁሉ ከፊቴ አስወግዱ፤ በደል መፈጸማችሁንም ተዉ። 17 መልካም ማድረግንም ተማሩ፤ ፍትሕ እንዳይጓደል አድርጉ፤ የተጨቈኑትን ታደጉ፤ አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች መብት ጠብቁ፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች አቤቱታ ስሙ።” 18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስቲ ኑና እንወያይ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ቢቀላ እኔ አጥቤ እንደ በረዶ ይጸዳል፤ እንደ ደም የቀላ ቢሆን እንደ ባዘቶ ይነጣል። 19 እሺ ብላችሁ ብትታዘዙኝ ምድር የምታስገኘውን በረከት ትበላላችሁ፤ 20 እምቢ ብትሉኝና ብታምፁ ግን ሰይፍ ይበላችኋል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ራሴ እግዚአብሔር ነኝ።” ኃጢአት የሞላባት ከተማ 21 ታማኝ የነበረችው ከተማ እንዴት እንደ አመንዝራ ሆነች! ቀድሞ ፍትሕ የሰፈነባትና የጻድቃን መኖሪያ ነበረች፤ አሁን ግን በነፍስ ገዳዮች የተሞላች ሆናለች። 22 ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፤ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ። 23 መሪዎችሽ ዐመፀኞችና የሌቦች ግብረ አበሮች ሆኑ፤ እያንዳንዱ ሁልጊዜ ገጸ በረከትና ጉቦ ይቀበላል፤ አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች መብት አይጠብቁም፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች አቤቱታ አይሰሙም። 24 ስለዚህ፥ የእስራኤል ኀይል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በጠላቶቼ ላይ ኀይለኛ ቊጣዬን አውርጄ ተቃዋሚዎቼን እበቀላለሁ። 25 በከባድ ቊጣዬ እቀጣሻለሁ፤ ከዝገትሽ አጠራሻለሁ፤ ርኲሰትሽንም በማስወገድ አነጻሻለሁ። 26 ቀድሞ የነበሩሽን ዐይነት ገዢዎችንና አማካሪዎችን አስነሣልሻለሁ፤ ከዚህ በኋላ ‘እውነት የሚገኝባት ታማኝ ከተማ’ ተብለሽ ትጠሪአለሽ።” 27 እግዚአብሔር እውነተኛ ስለ ሆነ ጽዮንን በፍርድ ያድናታል፤ በውስጥዋ ከሚኖሩት መካከል ንስሓ የሚገቡትን ይታደጋል። 28 ኃጢአተኞችንና ዐመፀኞችን ግን በአንድነት ሰባብሮ ይደመስሳል፤ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ሁሉ ይጠፋሉ። 29 በወደዳችሁት የአድባር ዛፍ ታፍሩበታላችሁ፤ በመረጣችሁትም የአትክልት ቦታ የኀፍረት መልክ ይታይባችኋል። 30 በመጨረሻም ቅጠሉ እንደ ረገፈ የወርካ ዛፍና ውሃ እንደሌለው የአትክልት ቦታ ትሆናላችሁ። 31 ገለባ በእሳት ብልጭታ እንደሚጋይ “ኀይለኞች ነን” የሚሉ ሰዎች ይጠፋሉ፤ እንደ ቃጠሎ እሳት በእነርሱ ላይ የሚመጣውን ጥፋት የሚያቆም የለም። |