Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሆሴዕ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ለንስሓ መጥራቱ

1 ሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “ኑ! ወደ እግዚአብሔር እንመለስ! እርሱ እንደ ሰበረን ይፈውሰናል፤ እርሱ እንዳቈሰለን ቊስላችንን ይጠግናል።

2 በፊቱ በሕይወት እንኖር ዘንድ፥ ከሁለት ቀን በኋላ ያድሰናል፤ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል፤

3 ኑ፤ እግዚአብሔርን እንወቅ፤ ሳናወላውልም እንከተለው፤ እርሱም እንደ ንጋት ብርሃንና ምድርን እንደሚያረካ የበልግ ዝናም በእርግጥ ወደ እኛ ይመጣል።”

4 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! እናንተን ምን ላድርጋችሁ? እናንተ ለእኔ ያላችሁ ፍቅር እንደ ማለዳ ጉምና እንደ ጠዋት ጤዛ ፈጥኖ ይጠፋል።

5 በነቢያቴ አማካይነት እንደማጠፋቸው በቃሌም አማካይነት እንደምገድላቸው አስጠነቀቅኋቸው፤ ስለዚህ ፍርዴ እንደ ንጋት ብርሃን ያንጸባርቃል።

6 እኔ ከመሥዋዕት ይልቅ የማይለዋወጥ ፍቅርን እወዳለሁ፤ ከሚቃጠል መሥዋዕት ይልቅ እኔን እግዚአብሔርን ማወቃችሁን እመርጣለሁ።

7 “እነርሱ ወደ አገሪቱ በገቡ ጊዜ ‘አዳም’ በምትባል ቦታ ከእኔ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፈረሱ፤ ለእኔ የማይታመኑ መሆናቸውንም ገለጡ።

8 ገለዓድ ክፉ ሰዎችና በደም የተበከሉ ነፍሰ ገዳዮች የሞሉባት ከተማ ሆናለች!

9 ወንበዴዎች ሰውን ለመግደል እንደሚያደቡ የካህናቱም ቡድን እንዲሁ ያደርጋል፤ ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ እንኳ እያደቡ ሰውን ይገድላሉ፤ አሳፋሪም የሆነ ወንጀል ይፈጽማሉ።

10 እጅግ የሚያሠቅቅ ነገር በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ አይቼአለሁ፤ ይኸውም ሕዝቡ ጣዖትን በማምለክ ዝሙት ረክሶአል።

11 “እናንተ የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! በእናንተም ላይ የፍርድ ቀን ወስኜአለሁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios