Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሆሴዕ 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሆሴዕ የእስራኤል ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ መጠየቁ

1 የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በኃጢአታችሁ ምክንያት የተሰናከላችሁ ስለ ሆነ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ።

2 የኑዛዜ ቃል ይዛችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እንዲህም በሉት፦ “ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤ በምሕረት ተቀበለን፤ እኛም የአንደበታችን መልካም ፍሬ የሆነውን ምስጋና እናቀርብልሃለን።

3 አሦር አያድነንም፥ በጦር ፈረሶችም አንታመንም፤ ከእንግዲህ ወዲህ በእጃችን የሠራነውን ጣዖት ሁሉ ‘አምላክ’ ብለን አንጠራም፤ አምላክ ሆይ! ወላጆቻቸው የሞቱባቸው በአንተ ምሕረትን ያገኛሉ።”


ለአዲስ ሕይወት ተስፋ መሰጠቱ

4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የሕዝቤን አለመታመን ፈውሼ፤ ወደ እኔ እመልሳቸዋለሁ ቊጣዬ ከእነርሱ ስለ ተመለሰ፥ እኔ በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ፤

5 ለእስራኤል ሕዝብ እንደሚወርድ ጠል እሆናለሁ። እነርሱ እንደ አበባ ይፈካሉ፤ እንደ ሊባኖስ ዛፎችም ሥር ይሰዳሉ።

6 ቡቃያዎቻቸው ይለመልማሉ፤ እንደ ወይራ ዛፍ የሚያምሩ ይሆናሉ፤ እንደ ሊባኖስ ደን መልካም መዓዛ ይሰጣሉ።

7 ተመልሰውም በእኔ ጥላ ሥር ይሆናሉ፤ እንደ እህል ቡቃያ ይለመልማሉ፤ እንደ ወይን ተክልም ያብባሉ፤ መዓዛቸውም እንደ ሊባኖስ የወይን ጠጅ ዝነኛ ይሆናል።

8 የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እኔ ከጣዖቶች ጋር ምን ግንኙነት አለኝ? ለጸሎታችሁ መልስ የምሰጥና የምንንከባከባችሁ እኔ ነኝ፤ እኔ ዘወትር ለምለም ሆኖ እንደሚታይ የጥድ ዛፍ ነኝ፤ ፍሬያማ የምትሆኑትም በእኔ አማካይነት ነው።”


መደምደሚያ

9 ጥበብ ያላቸው እነዚህን ነገሮች ይረዳሉ፤ አስተዋዮችም ያውቋቸዋል፤ የእግዚአብሔር መንገድ ትክክል ነው፤ ጻድቃን ይሄዱበታል፤ ኃጢአተኞች ግን ይሰናከሉበታል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios