ሆሴዕ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበእስራኤል ላይ የተወሰነ የመጨረሻ ፍርድ 1 የኤፍሬም ነገድ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ከፍ ብሎ በነበረበት ዘመን ሲናገር የሚሰሙት ሁሉ ይንቀጠቀጡ ነበር፤ በኋላ ግን ባዓል ለተባለ ጣዖት በመስገድ ኃጢአት ስለ ሠራ በሞት ተቀጣ። 2 አሁንም በጥበባቸው የቀለጡ ምስሎችና በብር የተሠሩ ጣዖቶችን በመሥራት በኃጢአት ላይ ኃጢአትን ይጨምራሉ፤ እነዚህ ሁሉ የሰው እጅ ሥራ ናቸው፤ ለእነዚህም የሰው እጅ ሥራዎች መሥዋዕት አቅርቡ ይላሉ፤ ሰዎችም በጥጃ መልክ የተሠሩ ጣዖቶችን ይሳለማሉ። 3 በዚህም ምክንያት እነርሱ እንደ ማለዳ ጉም ተነው ይጠፋሉ፤ እንደ ጠዋት ጤዛም ይረግፋሉ፤ ከአውድማ ላይ በዐውሎ ነፋስ እንደሚጠረግ እብቅ ወይም በጢስ መውጫ ወጥቶ እንደሚያልቅ ጢስ ይሆናሉ። 4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ አምላካችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የላችሁም፤ አዳኛችሁም እኔ ብቻ ነኝ። 5 ድርቅ በበዛበት በረሓ እንክብካቤ ያደረግኹላችሁ እኔ ነኝ። 6 ነገር ግን ወደ መልካሚቱ ምድር በገባችሁ ጊዜ እስክትጠግቡ በልታችሁ እጅግ ታበያችሁ፤ እኔንም ረሳችሁ። 7 ከዚህ የተነሣ እንደ አንበሳና በመንገድ እንደሚያደባ ነብርም እሆንባችኋለሁ። 8 ግልገሎችዋ የተወሰዱባት ድብ እንደምታደርግ እኔም አደጋ እጥልባችኋለሁ፤ እቦጫጭቃችሁማለሁ፤ እንደሚባላ አንበሳ እሆንባችኋለሁ፤ እንደሚበጣጥስ ክፉ አውሬም እበጣጥሳችኋለሁ። 9 “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በእኔ በምረዳችሁ ላይ ስለ ተነሣችሁ አጠፋችኋለሁ፤ 10 እናንተ ንጉሥና መሪዎች እንድሰጣችሁ ጠይቃችሁ ነበር፤ ታዲያ አሁን የሚያድናችሁ ንጉሥ፥ የሚከላከሉላችሁስ መሪዎች የት አሉ? 11 በቊጣዬ ነገሥታትን ሰጥቻችሁ ነበር፤ ነገር ግን በከፍተኛ ቊጣዬ አጠፋኋቸው። 12 “የእስራኤል ኃጢአትና በደል ተጽፎ ተከማችቶአል። 13 እስራኤል በሕይወት የመኖር ተስፋ አለው፤ ነገር ግን የሚወለድበት ጊዜ ሲቃረብ ከእናቱ ማሕፀን ለመውጣት እንደማይፈልግ ሕፃን ሞኝ ሆኖአል። 14 ከሲኦል ኀይል እታደጋቸዋለሁን? ከሞትስ አድናቸዋለሁን? ሞት ሆይ! መቅሠፍቶችህ የት አሉ? ሲኦል ሆይ! አጥፊነትህ የት አለ? እኔኮ አልራራላቸውም፤ 15 በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆንም የእግዚአብሔር ቅጣት የሆነው የምሥራቁ ነፋስ ከምድረ በዳ ተነሥቶ ይመጣል፤ ምንጩ ይቆማል፤ ወንዙም ይደርቃል። ነፋሱም የነበሩትን ውድ ዕቃዎች ሁሉ ገፎ ይወስድበታል። 16 ሰማርያ በእኔ ላይ በማመፅዋ በሠራችው በደል ተጠያቂ ትሆናለች፤ ሕዝብዋም በጦርነት ይሞታሉ፤ ሕፃናት በምድር ላይ ይፈጠፈጣሉ፤ እርጉዞችም ሆዳቸው ይሰነጠቃል።” |