Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዕብራውያን 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የምድራዊው ቤተ መቅደስ አገልግሎት

1 የመጀመሪያው ኪዳን የአምልኮ አገልግሎት ሥርዓትና ምድራዊ መቅደስ ነበረው፤

2 ሁለት ክፍሎች ያሉአት ድንኳን ተዘጋጅታ ነበር። መቅረዙና ጠረጴዛው፥ የመሥዋዕቱም ኅብስት የነበረባት መጀመሪያይቱ ክፍል “ቅድስት” ትባል ነበር።

3 ከሁለተኛው መጋረጃ በስተኋላ የምትገኘው ውስጠኛዋ ክፍል “ቅድስተ ቅዱሳን” ትባል ነበር።

4 በዚህችኛዋ ክፍል ውስጥ የወርቅ ማዕጠንትና በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ታቦት ነበሩባት፤ ከዚህችም የኪዳን ታቦት ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብ፥ ለምልማ የነበረችው የአሮን በትር፥ ዐሥሩ ትእዛዞች የተጻፉባት ጽላት ነበሩ።

5 በታቦትዋም ላይ ያለውን የኃጢአት ማስተስረያ መክደኛ በክንፋቸው የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ ነገር ግን ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሁን በዝርዝር መናገር አንችልም።

6 ሁሉ ነገር በዚህ ሁኔታ ከተዘጋጀ በኋላ ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ወደ ድንኳኒቱ መጀመሪያ ክፍል ዘወትር ይገባሉ።

7 ወደ ሁለተኛዋ ውስጠኛ ክፍል የሚገባው ግን የካህናቱ አለቃ ብቻ ነው፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ቀን ብቻ ነው፤ እርሱም ስለ ራሱ ኃጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም።

8 የመጀመሪያይቱ ድንኳን እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና ያልተገለጠ መሆኑን መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዐይነት ያሳያል።

9 ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፤ በዚህ ዐይነት የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የአቅራቢውን ሰው ኅሊና ፈጽመው ሊያነጹት አይችሉም፤

10 እነዚህ ነገሮች የመታደስ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ በሥራ ላይ የዋሉ አፍአዊ ሥርዓቶች ናቸው፤ እነርሱ ስለ መብልና ስለ መጠጥ፥ ስለ ልዩ ልዩ የመንጻት ሥርዓቶችም ብቻ የተደረጉ ናቸው።

11 ነገር ግን ክርስቶስ በመምጣት ላይ ላሉት መልካም ነገሮች የካህናት አለቃ ሆኖ ተገልጦአል፤ እርሱ የገባባት ድንኳን ትልቅና ፍጹም ናት፤ ይህች ድንኳን በሰው እጅ ያልተሠራችና ከዚህ ፍጥረት ያልሆነች ናት።

12 እርሱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አንዴ በማያዳግም ሁኔታ የራሱን ደም ይዞ ገባ እንጂ የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አልገባም፤ በዚህም ዐይነት የዘለዓለም ቤዛን አስገኘልን።

13 የፍየሎችና የወይፈኖች ደምና ለመሥዋዕት የተቃጠለች ጊደር ዐመድ በረከሱ ሰዎች ላይ ሲረጭ ከሥጋዊ ርኲሰት አንጽቶ የሚቀድሳቸው ከሆነ፥

14 በዘለዓለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር የሌለበት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናገለግል ኅሊናችንን ከሞተ ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!

15 እነዚያ የተጠሩት እግዚአብሔር በተስፋ የሰጠውን ዘለዓለማዊ ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ማእከላዊ አስማሚ ሆኖአል፤ ይህም የሆነው ሰዎችን በመጀመሪያው ቃል ኪዳን ሥር ሆነው ከሠሩት ኃጢአት ለማዳን እርሱ በመሞቱ ነው።

16 ኑዛዜ ሲኖር የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤

17 የኑዛዜ ቃል የሚጸናው ተናዛዡ ከሞተ በኋላ ነው፤ ተናዛዡ በሕይወት ካለ ግን የኑዛዜው ቃል ዋጋ አይኖረውም።

18 በዚህ ምክንያት የመጀመሪያው ኪዳን እንኳ ያለ ደም የጸና አይደለም።

19 በመጀመሪያ ሙሴ የሕጉን ትእዛዞች ለሕዝቡ ሁሉ ነገረ፤ ከዚህ በኋላ የወይፈኖችንና የፍየሎችን ደም ከውሃ ጋር አድርጎ የሕጉን መጽሐፍና ሕዝቡን ሁሉ በሂሶጵና በቀይ የበግ ጠጒር ረጨ፤

20 የረጨውም “እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የቃል ኪዳን ደም ይህ ነው” ብሎ ነው።

21 እንዲሁም በድንኳኒቱና በመገልገያ ዕቃ ሁሉ ላይ ደምን ረጨ።

22 በእርግጥም በሙሴ ሕግ መሠረት ከጥቂት ነገር በቀር ሁሉም ነገር በደም ይነጻል፤ ደም ካልፈሰሰም የኃጢአት ስርየት አይገኝም።


የክርስቶስ መሥዋዕትነት ኃጢአትን የሚያስወግድ መሆኑ

23 እንግዲህ እነዚህ የሰማያዊ ነገሮች ምሳሌ የሆኑት ሁሉ በዚህ ዐይነት ሥርዓት መንጻት ያስፈልጋቸው ነበር፤ ከሰማይ የሆኑት ነገሮች ግን ከዚህ በሚበልጥ መሥዋዕት መንጻት ያስፈልጋቸዋል።

24 ክርስቶስ የእውነተኛይቱ “መቅደስ” ምሳሌ ወደ ሆነችውና በሰው እጅ ወደተሠራችው ቅድስተ ቅዱሳን አልገባም፤ እርሱ አሁን ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት ወደ ሰማይ ገባ።

25 የአይሁድ የካህናት አለቃ የራሱ ያልሆነውን ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባ ነበር፤ ክርስቶስ ግን ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ አልገባም።

26 እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ መቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ኃጢአትን ለማስወገድ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ አንዴ በማያዳግም ሁኔታ ተገልጦአል።

27 ለሰው አንድ ጊዜ መሞት ተመድቦለታል፤ ከሞት በኋላም ፍርድ አለበት።

28 እንዲሁም ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ለማስወገድ አንድ ጊዜ ተሠውቶአል፤ ደግሞም ኃጢአትን ለመሸከም ሳይሆን እርሱን የሚጠባበቁትን ለማዳን ሁለተኛ ጊዜ ይገለጣል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios