Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዕንባቆም 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር ለዕንባቆም የሰጠው መልስ

1 በጥበቃ ቦታዬ እቆማለሁ በግንቡ ጫፍ ላይም ቦታዬን እይዛለሁ፤ እግዚአብሔር ምን እንደሚለኝ ለጥያቄዬም ምን መልስ እንደሚሰጥ እጠባበቃለሁ።

2 እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፦ “የምገልጥልህን ራእይ ጻፍ፤ በቀላሉ እንዲነበብም አድርገህ በሰሌዳ ላይ ቅረጸው፤

3 ምክንያቱም ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ይጠብቃል፤ እርሱም የሚናገረው የሚፈጸምበትን ቀን ነው፤ ሐሰትም የለበትም፤ ጊዜ የሚወስድ ቢመስልም ጠብቅ፤ በእርግጥ ይደርሳል፤ አይዘገይምም።

4 ትዕቢተኞችን ተመልከት፤ አስተሳሰባቸው ቅን አይደለም፤ ጻድቃን ግን በእምነታቸው ይኖራሉ።”


የክፉ ሰዎች አወዳደቅ

5 በእርግጥ ሀብት ሰውን ያታልላል፤ ትምክሕተኛ ሰው ዕረፍት የለውም፤ እንደ መቃብር ስስታም እንደ ሞትም በቃኝ የማይል ስለ ሆነ መንግሥታትን ሁሉ ለራሱ ይወራል፤ ሕዝቦችንም ይማርካል።

6 ሰው ሁሉ እንደነዚህ ባሉት ሰዎች ላይ በመሳለቂያ እንቆቅልሽ እንዲህ ይላል፦ “ያንተ ያልሆነውን የምታግበሰብስ ወዮልህ! በመያዣነት በተወሰዱ ዕቃ ራስህን የምታበለጽገው እስከ መቼ ነው?”

7 ባለ ዕዳዎቻችሁ በድንገት አይነሡምን? ተነሥተውስ አያርበደብዱአችሁምን? ከዚያ በኋላ እናንተ የእነርሱ ምርኮኞች ትሆናላችሁ።

8 የብዙ ሕዝቦችን ንብረት ስለ ዘረፋችሁ ከእነርሱ የተረፉት የእናንተን ንብረት ይዘርፋሉ፤ ይህም የሚሆነው እናንተ ሰዎችን ስለ ገደላችሁ፥ ምድሪቱን ከተሞችንና በእነርሱ የሚኖሩትን ስላጠፋችሁ ነው።

9 አደጋ እንዳይደርስበት መኖሪያውን ከፍ ባለ አምባ ላይ የሚመሠርትና በሕገ ወጥ ገቢ ቤቱን ለሚሠራ ወዮለት!

10 ተንኰልን ዐቅደህ ብዙ ሰዎችን በመግደል በቤትህ ኀፍረትን አምጥተሃል፤ ሕይወትህንም ለአደጋ አጋልጠሃል።

11 የግንቡ ድንጋዮች ከግድግዳው ይጮኻሉ፤ የእንጨት ምሰሶችም ይህንኑ ከውስጥ ያስተጋባሉ።

12 ሰውን በመግደል ከተማን ለምትቈረቊሩና፥ በበደል ዋና ከተማን ለምትሠሩ ወዮላችሁ!

13 ሰዎች የሚሠሩት ለቃጠሎ፥ መንግሥታትም የሚደክሙት ምንም ጥቅም ለሌለው ነገር እንዲሆን የሚያደርግ የሠራዊት አምላክ አይደለምን?

14 ባሕር በውሃ የተሞላ እንደ ሆነ ሁሉ፥ ምድርም የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ የተሞላች ትሆናለች።

15 ኀፍረተ ሥጋው ሲገለጥ ለማየት ለሰው ቊጣህን እንደ ጠንካራ መጠጥ የምትሰጥና እስኪሰክርም ድረስ የምታጠጣው አንተ ሰው ወዮልህ!

16 አንተ ራስህ ጠጥተህ በመስከር ትንገዳገዳለህ፤ አንተም በተራህ በክብር ፈንታ ውርደትን ትለብሳለህ፤ እግዚአብሔር ኀይለኛ የቅጣት ጽዋ እንድትጠጣ ያደርግሃል፤ ክብርህን ወደ ውርደት ይለውጣል።

17 በሊባኖስ ላይ ያደረስከው ዐመፅ ይደርስብሃል፤ በእንስሶች ላይ ያደረግኸው ጥፋት ያስደነግጥሃል፤ ይህም የሚሆነው ሰውን ስለ ገደልክ፥ አገሮችንና ከተሞችን፥ በእነርሱም ውስጥ ያለውን ሁሉ ስላጠፋህ ነው።

18 ኧረ ለመሆኑ የጣዖት ጥቅሙ ምንድን ነው? እርሱ እኮ በሰው እጅ ተቀርጾ የተሠራ ነገር ነው፤ ከሐሰት በቀር ከእርሱ ምንም አይገኝም፤ ታዲያ እርሱን ቀርጾ የሠራው ሰው ምንም መናገር በማይችል በዚህ ጣዖት መታመኑ ምን ሊጠቅመው ነው?

19 ከእንጨት ተጠርቦ የተሠራውን ነገር “ንቃ!” ከድንጋይ ተቀርጾ የተሠራውንም ነገር “ተነሥ!” ለምትል ለአንተ ወዮልህ! ለመሆኑ ጣዖት አንዳች ምሥጢር ሊገልጥልህ ይችላልን? እነሆ ጣዖት በብርና በወርቅ ተለብጦ የተሠራ ነው፤ የሕይወት እስትንፋስ ግን ፈጽሞ የለውም።

20 እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ስለዚህ የዓለም ሕዝብ ሁሉ በፊቱ ጸጥ ይበል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios